የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪው የህውሃት ቡድን በመደምሰስ ድል ይጎናጸፋል-- የቀድሞው ሀገር መከላከያ ስራዊት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪው የህውሃት ቡድን በመደምሰስ ድል ይጎናጸፋል-- የቀድሞው ሀገር መከላከያ ስራዊት
ደሴ ሀምሌ 30/2013 (ኢዜአ) ለውጭ ጠላትና ወራሪ ሃይል ተንበርክኮ የማያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪው የህውሃት ቡድንን ባጭር ጊዜ በመደምሰስ ድል እንደሚጎናጸፍ አያጠራጥርም ሲሉ የቀድሞው ሀገር መከላከያ ስራዊት አባላት ተናገሩ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ስራዊት አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊ አባላት መካከል መቶ አለቃ መሰለ መኮነን እንደገለጹት እናት ሀገር ኢትዮጵያ ስትደፈር ተቀምጦ የሚመለከት ማንም ኢትዮጵያዊ የለም፡፡
በዚህም አሸባሪው ህወሓት የጀመረውን አማራን በማጥፋት አገር የማፍረስ ውጥን ሴራ በጋራ መስዋትነት በመክፈል ለማክሸፍ በአንድነት የምንቆምበት ጊዜ አሁን መሆኑን ገልጸዋል።
"የኢትዮጵያ ህዝብ ለውስጥ ተላላኪ ቀርቶ ለውጭ ጠላትም የሚበረከክ አደለም" ያሉት መቶ አለቃ መሰለ “አንድነታችንን አጠናክረን ጠላትን ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ዝግጁ ነን” ብለዋል፡፡
አባለቱን አስተባብረው ወደ ግንባር ለመዝመት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው “ነጻነቷና ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ለዘመናት የኖረች ሀገር በአሸባሪ ሽፍታ አትፈርስምም” ብለዋል፡፡
ሌላው የውይይቱ ተሳታፊና የደሴ ከተማ ነዋሪ ሃምሳ አለቃ አሊ ሰይድ በበኩላቸው "ሀገር በባንዳ፤ አውሬ ቡድን ተወራ ከማየት ሞቴን እመርጣሁ" ብለዋል፡፡
"አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ ልጄን፤ ሚስቴንና ሀብቴን ሳልል ካዛሬ ጀምሬ ግንባር ለመሄድ ዝግጁ ነኝ" ያሉት ሃምሳ አለቃ አሊ “በፊት ያገኘሁትን ሙያና ልምድ ተጠቅሜ ህዝብና አገሬን ነጻ አወጣለሁ” ብለዋል፡፡
“ቡድኑ መላውን የትግራይ ህዝብ ለማዝመት በመሞከር ጦርነቱን ህዝባዊ ለማድረግ እንደጣረው ሁሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ ግንባር ዘምቶ የአገሩን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ከታሪክ ተወቃሽነት መዳን አለበት” ብለዋል፡፡
“አሸባሪው ቡድን ሀገር ወዳድ ስራዊትን በትኖ ግፍ የፈጸመውን የቀድሞ ታሪኩን አሁንም በመከላከያ ሰራዊት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸም ሀገር ለማፍረስ የሚሰራው ዳግም ሰራዊቱን በትኖ ለስቃይ ለመዳረግ መሆኑ መታወቅ አለበት” ብለዋል።
በዚህም በእርሳቸው የደረሰው ግፍና በደል በአሁኑ ሰራዊት ላይ ዳግም እንዳይፈጸም በ2ኛ መካናይዝ ክፍለ ጦር ያገኙትን የመድፍና የታንክ አተኳኮስ ልምድ ተጠቅመው ቡድኑን ለመደምሰስ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡
የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በበኩላቸው እንደተናገሩት አሸባሪውን ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ በሚደረገው የህልውና ዘመቻ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያርገው ሁለተናዊ ተነሳሽነትና ድጋፍ የሚደነቅ ነው፡፡
“የቀድሞ የሀገር መከላከያ ስራዊት አባላትም እኛ እያለን አገር አትፈርስም በሚል ኢትዮጵያዊ ወኔ ወደ ግንባር ለመዝመት ያሳዩት ቁርጠኝነት ለሀገርና ለህዝብ ያላቸውን ፍቅር በተግባር ያሳየ ነው” ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም ከመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር ተቀናጅተው አገርን ከመፈራረስ እንዲታደጉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” ያሉት ከንቲባው “ሁሉም የሚችለውን በማድረግ የጋራ ጠላታችንን ማጥፋት ይኖርበታል” ብለዋል፡፡
“የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ በበኩላው አሸባሪው ህወሓት አማራን አዳክሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጀመረውን ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ እየተፋለመው ነው” ብለዋል፡፡
“ከውጪ ጠላቶቻችን ጋር ወግኖ አገር ለማፍረስ የሚያርገው እንቅስቃሴ እንደማይሳካለት ጠቁመው ህብረተሰቡ በሐሰት ወሬ ሳይደናገጥ የአካባቢውን ሰላምና አንድነት ከማስጠበቁም ባለፈ ወደ ግንባር ለመዝመት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል” ብለዋል፡፡
በውይይቱ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፤ የቀድሞው መከላከያ ስራዊት አባላትና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡