የሀገር ሕልውናን ለማስከር በግንባር የዘመቱ ቤተሰቦችን መንከባከብ የኛ ድርሻ ነው - ማህበረሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ሕልውናን ለማስከር በግንባር የዘመቱ ቤተሰቦችን መንከባከብ የኛ ድርሻ ነው - ማህበረሰቡ
መቱ፤ ነሐሴ 2/2013 (ኢዜአ) የሀገር ሉዓላዊነትና ሕልውና ለማስከበር በግንባር የተሰለፉ የዘማች ቤተሰቦችን መንከባከብ የኛ ሃላፊነት ነው ሲሉ በኢሉባቦር ዞን የመቱ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ እያደረጉት ያለው ድጋፍ የአሸባሪውን ሕወሓት የጥፋት ተልዕኮን ለመመከት ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ለመቆም ዘመቻውን ለተቀላቀሉ የዘማች ቤተሰቦች ነው።
የወረዳው ነዋሪ አቶ ታከለ ዲሳሳ ሕብረተሰቡን በማስተባበር ለሀገር ለቆሙ የሚሊሻ ቤተሰቦች ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው እንቆማለን ብለዋል።
የሚሊሻ ቤተሰቦችን በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ከመደገፍ ባሻገር ለሀገር ሕልውና ዘመቻው አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈልም ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ፍሬሕይወት ኢተፋ ይባላሉ የዘማች ድንገቱ ለገሰ ባለቤት ሲሆኑ "ባለቤቴ ለሀገር እና ለሕዝብ ለመቆም እንደሄደ ሕዝቡ ደግሞ ከጎናችን ቆሞ ሳይ ትልቅ ተስፋ ሆነውኛል ይላሉ።
አሁን እርሱ ትቶት የሄደው የእርሻ ሥራ በሕብረተሰቡ ተሠርቶላቸው ሲያዩም መደሰታቸውንና በችግር ጊዜ ሕብረተሰቡ ከጎናቸው ሆኖ ሲያዩ ትልቅ ተስፋ እንደሰነቁ ይናገራሉ።
ወይዘሮ አዛለች ከበደ በበኩላቸው የሀገሩን ሰላም ለማስከበር ለዘመተው ባለቤታቸው ሕብረተሰቡ እያደረገው ያለው ድጋፍ "እርሱ በመሄዱ የተለየ ሐሳብ እንዳይሰማን አድርጎናል" ብለዋል።
ሕብረተሰቡ በቤተሰብነት አብሮን እየተከታተለን ስለሆነና የግብርና ሥራዎችንም ስለሠሩልን ችግር ይገጥመናል የሚል የተለየ ስጋት አይገባንም በማለትም ተናግረዋል።
ምስጋና ብርሃኑ ደግሞ የዘማች ሚሊሻ ብርሃኑ ተካልኝ ልጅ ሲሆን አባቱ ቤተሰቡን ለማስተዳደር ሲሰራ የነበረው ሥራ በሕብረተሰቡ በትብብር እንደተሠራላቸው ይናገራል።
አባቴ ለሀገሩ ሰላም እንደቆመ ሁሉ ሕብረተሰቡ ለቤተሰቡ መቆሙን እያሳየን ነውም ብሏል።
በእስካሁኑ ድጋፍም ለ81ሚሊሻዎች ቤተሰቦች በ86 ሄክታር መሬት ላይ የማሳ ዝግጅት፣ የአረም ማረም፣ የማዳበሪያ መጨመር ሥራዎችን ጨምሮ የአምስት ቤተሰቦች ቤቶችም ታድሰዋል።
ይህም በገንዘብ ሲተመን የ116ሺህ ብር ግምት ያለው ሥራ መሠረቱን የገለፁት የመቱ ወረዳ አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸብር አለባቸው ናቸው።
በዚህም ለዘማች ልጆች የትምህርት መማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ቤቶቻቸውን ከመሥራትና ከማደስ በተጨማሪ ማሳቸውን ማረስ፣ በማሳ ላይ ያለውን ሰብል የማረም ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን የገለፁት የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ የወረዳው ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ ዩሱፍ ናቸው።