ኢትዮጵያዊ ከሃገሩ በላይ የሚሳሳለት ነፍስ የለውም ...‼

ያንተስራ ወጋየሁ (ዲላ ኢዜአ) 

እኛ ኢትዮጵያዊያን በሀገራችን ሉአላዊነት ላይ ከማንም ጋር አንደራደርም፣ክብራችንንም አሳልፈን አንሰጥም፣ይህን እውን ለማድረግ የምንሳሳለት ነፍስም የለንም። በተለይ ከሀዲ፣ዘራፊ፣ነውረኛ፣ ጮሌ፣ ዋሾ፣ ወንበዴና ዘረኛ ለሆነው ህወሓት አሸባሪ ቡድን።

ይህ ቡድን ህወሓት የሚል ስያሜ ይዞ ከተነሳበት ማግስት ጀምሮ ከስልጣን እስከተወገደበት ጊዜ ድረስህዝብን ለማገልገል የተነሳ ሳይሆን የማፍያ ስብስብ ስለመሆኑ የሀውዜንና ማይካድራን ጭፍጨፋን ማንሳት በቂ ነው።

ቡድኑ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት በሴራ ፖለቲካ ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት፣ በዜጎች ደም የስልጣን ጊዜውን ማራዘም ዋና ተግባሩ አድሮጎት ነበር።

የሴራ ፖለቲካውን ተረድቶ የሚቃወመውን ከማጥፋት ባለፈ ለአደጋ ጊዜ ትጥቅና ሰራዊት እንዲሁም የውሸት ፕሮፓጋንዳውን የሚያራግቡለት አፈ ቀላጤዎችን በየአለማቱ በማስቀመጥ ያጯጩሃል።

አሁን ላይም ለዘመናት ያከማቸውን ትጥቅና ስራዊት በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ቢነጠቅም ዛሬም በሞት አፋፊ ላይ ሆኖ እንኳን የሚነዛውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሚያስተጋቡ የጥቅም ተጋሪዎችን አላጣም።

በተለይ መሬት ላይ ካለው ሃቅ በተቃራኒ እንደ አይጥ በዋሻ ውስጥ እየተሽሎከሎከ እንኳን "ለወሬ ነገሪ ሳላስቀር ይህን ያክል ክፍለ ጦር ዶግ አመድ አደረኩ" እያለ ቅዥቱን ሲነዛ የሚያስተጋቡ ሚዲያዎችን መስማት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ብቻ ሳይሆን አሁንም እያደረጉት ያለ ተግባር ነው።

የተካነበትን የውሸት መረጃ መንዛት ስራው ያደረገው የጥፋት ቡድኑ ዛሬም ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት በሌላ ፕሮፓጋንዳ ብቅ ብሏል። 

ከጥቅም ተጋሪ ግለሰቦች አንስቶ ግብጽና ሱዳን እንዲሁም ትላላቅ የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን ጭምር የጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል ይጠቀሙበታልም።

በእርግጥ በቢሊዮን ኪዮብክ ሊትር ከማበደር አንስቶ ለአደጋ ጊዜያት በግድቦቿ ውሃ እስከመያዝ በደረሰ አስገዳጅ ስምምነቶች የተጠረነፈችው ሱዳን የግብጽ ድምጽ መሆኗ የሚጠበቅ ነው።

የጥፋት ቡዱኑ የጥቅም ተጋሪዎችን ጨምሮ ለቀይ ባህር የቀረቡ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ጠንካራ መንግስት መመስረታቸውና የመልማት ጅምራቸው ስጋት ውስጥ የሚከታቸው ምዕራባዊያን ካይሮን ጨምሮ በተለያየ የቅርብና የሩቅ ስፍራዎች በመሆን በሃገራችን ላይ ጫና ለመፍጠር እየሞከሩ መሆኑም ይታያል።

እነዚህ ሃይሎች እንበር ተጋዳላይ እያለ የሚጨፍሪውን ርዝራዥ ጨምሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን ካለው አሸባሪ ቡድን ጋር ወግነው መገኘታቸው የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል።

እስከ አሁን ድረስ ባደረገችው ጉዞ ኢትዮጵያ እያሸነፈች መሆኗ ደግሞ ይበልጥ የጥፋት ተልዕኳቸው ማስፈጸሚያ ላደረጉት አሸባሪ ቡድን አቅማቸው የፈቀደውን ያክል ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ከመጠራራት ባለፈ ፣ ዓይን ያወጣ ጥፋቱን በተደጋጋሚ እንዳላየ ማለፋቸው የነሱን ማንነትና ፍላጎት በግልጽ ያመላከተ ነው።

አሸባሪ ቡድኑ የራሴ ነው እያለ በሚናገርለት ህዝብ ላይ ርሃብና እልቂት እየደገሰ፣ ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ እያገደ፣ ህጻናትን ከእናቶች ጉያ በመንጠቅ ለጦርነት እየዳረገ እያዩት ከመውቀስ ይልቅ መንግስት የራሴ ህዝብ ተጎዳ ብሎ ያለ አቅሙን አሟጦ መጠቃቱን ችሎ አስፈላጊውን ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የሚያደርገውን ልፋት ማሳነስ ዋነኛ ተግባራቸው መሆኑም የዘመናችን አሳዛኝ ገጠመኝ ነው።

ይሁንና እኔ ለሀገሬ እቆማለሁ በሚል ከየአቅጣጫው የተመመው ኢትዮጵያዊ የአሸባሪው ህወሃት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በሀገር ውስጥ ሰሚ እንዳጣ ከማሳየቱም በላይ በሀገር ክብርና ሉአላዊነት የሚደራደር ዜጋ እንደሌለ ለጠላትም ለወዳጅም አስተምሯል።

በዲላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት እንደ ወይዘሮ አስቴር አለማየሁ ወጣት ልጃቸውን ለሀገራዊ ጥሪ በመላክ ሳይገደቡ ለሰራዊቱ ስንቅ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ሲሉ ማየት ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ክብርና ሉአላዊነት የሚሳሳው ነገር እንደሌለ አስረጂ ነው።

ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከተነሳን አይደለም ለወያኔ ያልተጨበጠ የሃሰት ውዥንብር ይቅርና በስልጣኔና በኢኮኖሚ ለፈረጠሙ የውጭ ወራሪዎች እጅ አለመስጠታችን ታሪክ ምስክር ነው” ይላሉ።

በሃገር ጉዳይ እናት ልጆቿን ለመስዋዕትነት ለማቅረብ እንደ ወይዘሮ አስቴር ሁሉ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ታላቅ ክብር መሆኑ የታየበት ሃገር የማዳን የህልውና ዘመቻው ከዳር እስከዳር በሁሉም ዘርፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ የኢትዮጵያን ልማትና ብልጽግና መቃረብ በጉልህ የሚያሳይ ነው። 

በአገዛዝ ዘመኑ ሃገር አፍርሼ ጨርሻለሁ ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት አንድነት በህዝቡ ውስጥ አይኖርም በሚል የተሳከረ ሂሳባዊ ስሌት እራሱን ቆልሎ የነበረው አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያዊያን ከየትኛውም ጫፍ ላይ ሆነው በሃገራቸው ጉዳይ ግንባራቸውን እንደማይመልሱ ሲረዳ የሞት ሞቱን በተለያዩ መልኮች የጥፋት ተልዕኮውን ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ ቢገኝም አይሳካለትም ።

በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ላይ ለዘመናት ጥፋትን ሲፈጽም፣ ሲደግስ የኖረው ይሄ አሸባሪ ቡድን እኔ የለሁባትም ይልቁንም እሷን ለማፍረስ እስከ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ በማለት ያደረገው የቁልቁለት ጉዞ እሱና የሱ ተከፋዮች ድጋፍና አጋርነት የትም እንደማያደርሰው የሚመሰከርበት የህዝብና የሃገር ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጥበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየቀረበ መጥቷል።

ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ በግፍና በጅምላ ከመጨፍጨፍ ጀምሮ ለተዛባ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ሙታንን ክብር በመንሳት ለዓለም ለማሳየት የሚያደርገው ጥረትም አሳፋሪ ተግባር ነው። የእናት ጡት ነካሽ የሆነውን አሽባሪውን የህውሓት ቡድን ለማስቆም በተባበረ ክንድ መነሳታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በልጆቿ መስዋትነት እንደ ጥንቱ ሁሉ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች። ሠላም.. ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም