ቀጥታ፡

ለአገር መከላከያ ሰራዊት ያለንን አጋርነት አጠናክረን እንቀጥላለን ---የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ

ድሬዳዋ፣ነሐሴ 2/2013 (ኢዜአ) የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ የህወሃት የሽብር ቡድን ሃገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ በግንባር ለሚገኘው የሃገር መከላከያ ሰራዊት በደም ልገሳና የተለያዩ ድጋፎች በማድረግ አጋርነታቸውን ቀጥለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌትና የግድቡን ሁለንተናዊ ጥቅሞች ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ጉባኤና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል።

ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ምሁራን በግንባር የሃገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየታገለ ከሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ጎን መሆናቸውን ደም ከመለገስ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች እያሳዩ ነው።

"ደማችን ለመከላከያ ሠራዊታችን" በሚል መሪ ትላንት በተካሔደ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲው መምህር ግዛቴ ጌቴ "ለአገር ሉአላዊነትና ህልውና ህይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ደም ብቻ ሳይሆን ያለኝን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው በደም ልገሳ ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ከሚያደርጉት አጋርነት ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው መልካም ስነ-ምግባር የታነጹ ምሁራንን ከማፍራት ጎን ለጎን በሃገር ሉዓላዊነት መከበር ላይ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ንቁ ተሳታፊ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

ሌላው በደም ልገሳ መርሃ-ግብሩ ላይ የተሳተፉት የዩኒቨርሲቲው መምህር ዶክተር አለማየሁ ዘውዴ እንደተናገሩት አሁን ላይ ሃገራችን ፈታኝ ሁኔታ ላይ ትገኛለች።

ይሄንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በግንባር ለዘመተው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከደም ልገሳ በተጨማሪ በደመወዝና በማንኛውም ድጋፍ ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎና ብሔራዊ ምክር ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንደተናገሩት ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ የሕዳሴ ግድቡን እድሜና አገልግሎት ማሳደግ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርም የሕዳሴው ግድብና ሌሎች ወንዞችን በዘላቂነት ብልጽግናን እንዲያረጋግጡ ማገዝ መሆኑም ነው ያመለከቱት።

"ወንዞቻችን የኢትዮጵያን ከፍታ እንዲያመጡ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ማሳደግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን አለበት" ብለዋል፡፡ 

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና የበጎ አድራጎት ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ታደሰ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲዎች ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶችን ቀጣይነት ባለው መንገድ እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ችግኞችን ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ በማሳደግ ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣም አመልክተዋል።

በችግኝ ተከላና ደም ልገሳ መርሀ-ግብሩ ላይ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ አፈወርቅ ካሱን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎችና ምሁራን ተግኝተው ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም