የሠራተኛውን መብት በመጠበቅ የኢንዱስትሪ ሰላምና ልማት ማጠናከረ እንደሚገባ ተመለከተ

አዳማ ነሓሴ 3/2010 የሠራተኛውን የሙያ መብት፤ ደህንነትና ጤንነት በመጠበቅ የኢንዱስትሪ ሰላምና ልማትን ማጠናከር ማፋጠን እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ 15ኛው የክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች የዘርፉ ሴክተር ተቋማት ዓመታዊ የጋራ ጉባኤ "ተደምረን የኢንዱስትሪ ሠላምና የዜጎች ማህበራዊ ለውጥ እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል። የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም በጉባኤው መክፈቻ ወቅት እንደገለጹት በሥራ ቦታ የሰጥቶ መቀበል መርህ ባህል እንዲሆንና እንዲዳብር ማድረግ ለኢንዱስትሪ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህም ከአሰርና ሠረተኛ ብቻ ሳይሆን የዘርፉ ተቋማት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው የሠራተኛውን  የሙያ መብት ደህንነትና ጤንነት በመጠበቅ የኢንዱስትሪ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል። ለአሰርና ሠራተኛ የጋራ ተጠቃሚነት፣ ሀገራዊ ልማትና እድገት ቀጣይነት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸውን የሠራተኛ ማህበራት በየኢንዱስትሪው ተደራጅተው የመደራደርና የመተማመን ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲጎልብት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ለኢንዱስትሪው ልማት ዘላቂ ሠላምና እድገት ወሳኝ ሚና ያለውን የአሠሪና ሠራተኞች አዋጅ ላይ የባለድርሻ አካላትን ግብዓት ባከተተ መልኩ መሰረታዊ ማሻሻያ በማድረግ ለሚንስቴሮች ምክር ቤት መቅረቡንም አስታውቀዋል። አዲስ የተሻሻለው አዋጅ በአምራች ድርጅቶች የሚሰሩ ሠራተኞች የዝቅተኛ ደመውዝ  ክፍያ የመወሰን፣ ተቋማዊ አደረጃጀት የመዘርጋትና ኮሚሽን እንዲቋቋም ይደነግጋል። በዚህም ከሀገር ውስጥ የሥራ ሥምሪት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የሠረተኛና አሰሪዎች መብትና ጥቅም ማስጠበቅ ጉዳይ በዘላቂነት ምላሽ እንደሚያገኝ ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል። በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ካልተቻለ የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሠላምና ዕድገት ማስቀጠል እንደማይቻል የገለጹት ደግሞ የሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ናቸው። "ወደ ሥራ እየገባ ያለውን ሰፊውን የሰው ኃይል በአግባቡ አደራጅተን መብትና ጥቅሙን  በማስጠበቅ የኢንዱስትሪ  ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግ ይጠበቅብናል" ብለዋል። በአብዛኛው የቻይና ካምፓኒዎች፣ በቦሌ ለሚና የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች  ውስጥ ሠራተኞችን በማህበር ማደራጀት እንዳልተቻለ ያመለከቱት ፕሬዝዳንቱ በዚህም የሠራተኞች የሙያ ደህንነት፣ ጤንነትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሠራተኛው ሰለሚሠራው ሥራ በቂ ክህሎትና ግንዛቤ ሳይኖረው እንዲሰራ በመደረጉ ዜጎች ለጉዳት እንደሚዳረጉ ጠቅሰው የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የውጭ ካምፓኒዎች የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ተግባራዊ እንዲያደርጉ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል። የኢትዮዽያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢንጅነር ጌታሁን ሁሴን በበኩላቸው የዜጎች የመደራጀት፣ የመሰብሰብና ሰብዓዊ መብታቸውን ማክበር ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግና የሀገሪቱን እድገት ለማፋጠን የሁሉንም መብትና ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ዘላቂ የሆነ  የአሰራርና አደረጃጀት መዋቅር መዘርጋት ተገቢነት እንዳለውም ጠቁመዋል። ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው ጉባኤ የአሰሪዎች እና ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽኖች፣ የዘጠኝ ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች አመራሮች ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም