በአፋር ክልል ሶስት ቀበሌዎች የጎርፍ አደጋ ተከሰተ

196

ሰመራ፤ነሐሴ 2/2013(ኢዜአ)በአፋር ክልል አዉሲ-ረሱዞን አይሳኢታ ወረዳ በአዋሽ ወንዝ ሙላት በሦስት ቀበሌዎች የጎርፍ አደጋ መከሰቱን የክልሉ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሀፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤት የቅድመ-ማስጠንቀቅና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን ለኢዜአ እንደተናገሩት ከሃምሌ 28/2013 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳዉ ሦስት ቀበሌዎች የአዋሽ ወንዝ ሰብሮ በመውጣት ጎርፍ አስከትሏል።

“አደጋው ቀድሞ በተከናወኑ የቅድመ-ጥንቃቄቅ ስራዎች ህብረተሰቡ ከአካባቢዉ እንዲወጣ በመደረጉ የተፈናቀሉ ሰዎች ከመቶ አባዋራዎች የማይበልጡ ሲሆን በተጨማሪም ጎርፍ 50ሄክታር መሬት በሚሆን የእርሻ መሬት ላይ ጉዳት አድርሷል” ብለዋል። 

ጎርፍ የተከሰተባቸዉ ቀበሌዎች የከርቡዳ፣ ኮሎዱራና ሂነሌ ቀበሌዎች ሲሆኑ ጎርፉ የሰበረበትን አካባቢ ለመዝጋት ከሚመለከተዉ የተፋሰስ ባለሰልጣን ጋር በመሆን ርብርብ እየተደረገ ነዉ” ብለዋል።

በክረምቱ ከፍተኛ ዝናብ እየተመዘገበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በክልሉ የአዋሽ ወንዝን ተከትለዉ በሚገኙ 10 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ እንደሚከሰት ይጠበቃል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ቀደም ሲል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።

በተለይም በነዚህ ወረዳዎች ስር የሚገኙ 40 ቀበሌዎችን ጨምሮ ከአጎራባች ከፍተኛ ቦታዎች የሚነሱ ተፋሰሶች ምክንያት በነዚህ አካባቢዎች ከ90ሺ ሰዎች በላይ የጎርፍ ተጠቂዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በመሆኑም የህብረተሰቡን የጎርፍ አደጋ ተጠቂነት ለመቀነስ በየጊዜዉ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ለጎርፍ አዳጋ በማያጋልጡ ቦታዎች እንዲሰፍር የማድረግ ስራዎች በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን በማሳተፍ ለማስፈጸም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከነዚህ የጎርፍ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ዉስጥ በታችኛዉ አዋሽ አዋሳኝ የሚገኘዉ የአይሳኢታ ወረዳ አንዱና ዋነኛዉ ሲሆን ያለፈዉ አመትን ጨምሮ በወረዳዉ ስር የሚገኙ ብዙ ቀበሌዎች የጎርፍ አደጋ በተደጋጋሚ የሚጠቁ ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም ጽህፈት ቤቱ ካለፉት አመታት ተሞክሮ በመዉሰድ ከዚህ በፊት በሚከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች የሰዎችን ህይወት የመታደግ ስራዎች በሚፈለገው ደረጃ በፍጥነት ለማከናወን የጀልባዎች እጥረት በዋናነት የሚጠቀስ እንደነበረ አንስተዋል።

በዚህ አመት ቢሮዉ ከ4ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እሰከ 40 ኩንታል የመጫን አቅም ያለዉ አራት የሞተር ጀልባዎች ግዢ ፈጽሞ ለሞተረኞች ተገቢዉ የአደጋ ጊዜ ህይወት አድን ስራና ተያያዥ ስልጠና ተሰጥቷቸዉ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቀነስ ተጨማሪ ዝግጅት ተደርጎል ብለዋል።

በአፋር ክልል ባለፈዉ አመት በአዋሽ ወንዝ አዋሳኝ አካባቢዎች ተክስቶ በነበረዉ የጎርፍ አደጋ ከ280ሺ በላይ ሰዎች መጎዳታቸዉን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም