ቀጥታ፡

ወጣቶች ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን የሚቆሙት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስከብረው ለማስቀጠል ነው - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ነሐሴ 02 ቀን 2013 (ኢዜአ) “ወጣቶች ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን የሚቆሙት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስከብረው ለማስቀጠል ነው” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከአዲስ አበባ ከተማና በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተውጣጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች የተሳተፉበት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሰልፍ በመስቀል አደባባይ ሰልፍ እየተካሄደ ይገኛል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባዋ፤  ኢትዮጵያውያን ማን ሊያስተዳድራቸው እንደሚችል መወሰናቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያውያን ድምጽ መከበር እንዳለበት አስገንዝበው፤ በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት ማስቀመጥ እንደማይቻል አስረግጠዋል።

“ኢትዮጵያን የሚመራት ኢትዮጵያውያን የመረጡት መሪ እንጂ፤ ሌሎች የሚያስቀምጡልን አሻንጉሊት መንግስት አይደለም” ብለዋል።

ኢትዮጵያን የሚመራት ኢትዮጵያውያን ሁሉንም ተጽዕኖ ተቋቁመው የመረጡት መንግስት ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል።

በመሆኑም ከዚህ ከኢትዮጵያውያን ፍላጎት በተቃራኒ እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ ሃይሎች ከኢትዮጵያ ህዝቦች ፍላጎት ጎን እንዲቆሙ ምክትል ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።

ለፍትሃዊነትም ድምጻቸውን እድያሰሙ ጠይቀዋል።

ከመከላከያ ሰራዊት ጎን መቆማቸውን ለመግለጽ ዛሬ በመስቀል አደባባይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን የሚያሰሙት ድምጽ ኢትዮጵያ ስትነካ አንድነቷ ይጠነክራል የሚለውን እንደሚያሳይም አስገንዝበዋል።

“የመከላከያ ሰራዊታችንና መላው የጸጥታ ሃይላችን ለኢትዮጵያ ክብር ተመን የማይገኝለት ዋጋ እየከፈለ ነው” ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ “ታላቅ ክብር ይገባዋል፣ እንደግፋቸዋለን፣ አብረናቸውም እንቆማለን” ሲሉ ገልጸዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱን ለመቀላቀል ወጣት የኢትዮጵያ ልጆች ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ መሰለፋቸውን ጠቅሰዋል።

“ወጣቶች ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን የሚቆሙበት ዋና ምክንያት አሸባሪውን ህወሃት ለመደምሰስ ብቻ ሳይሆን ጸረ-ኢትዮጵያ ሃይሎችን ሁሉ ለመደምሰስና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስከብረው ለማስቀጠል እንጂ” ብለዋል።

“ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀን ህዝቦች ነን” ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ “የኢትዮጵያ ጀግንነት ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ አንድነቷም ከብረት ይጠነክራል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም