ቀጥታ፡

የአሸባሪው ህወሓት ጭካኔ ማሳያ

አብዱራህማን ናስር

ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በማይካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በድርጊት አፈፃፀሙም ሆነ በተጎዱ ሰዎች ብዛት እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽመዋል ከሚባሉ አሰቃቂ  ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ሁሉ በእጅጉ የከፋ መሆኑን የመብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ። በማይካድራ የተፈጸመው ክስተት በሰው ዘር ላይ የተፈጸመ አሰቃቂና ሊታመን የማይችል አረመኔያዊ ድርጊት ስለመሆኑም ብዙዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ቡድን በአካባቢው ተገኝቶ ያገኘውን መረጃ መሰረት አድረጎ ባወጣው ሪፖርት በማይካድራ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ ሌሊቱን ሙሉ በተፈጸመው ማንነትን መሰረት ባደረገ ጅምላ ጭፍጨፋ ከ600 በላይ የሆኑ ሰዎች ተገድለዋል። ጥቃቱን ያደረሱት የአሸባሪው የህወሓት ታጣቂዎች እና ሳምሪ በመባል የሚታወቁ ወጣቶች መሆናቸውን በሪፖርቱ ይፋ ተደርጓል።

እነዚህ አካላት በእያንዳንዱ ቤት እየገቡ በመታወቂያ ካርድ እየለዩ በአማራዎችና ወልቃይቴዎች ብለው በለዩዋቸው እንዲሁም የትግራይ ተወላጅ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ጭምር ጭፍጨፋ ፈጽመዋል።  በጥቃቱ ወቅት በስልጣን ላይ የነበረው የከተማው የጸጥታ መዋቅር ሲቪል ሰዎችን ከአደጋና ጥቃት ከመከላከል ይልቅ፤ በተቃራኒው ሳምሪ ከሚባለው የወንጀሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ የወጣቶች ቡድን ጋር እያበረና እየተባበረ ጥቃቱን ፈጽሟል።

በሰዎቹ ላይ የተፈጸመው ግድያ ከፍተኛ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት እንደነበር የሚያመለክተው የኮሚሽኑ ሪፖርት በዱላ በመደብደብ፣ ስለት ባለው መሳሪያ በመውጋት፣ በገጀራና በፋስ፣ በመጥረቢያ በመምታትና በገመድ በማነቅ ግድያ ፈጽመዋል። የጭፍጨፋ ግድያውን ሲፈጽሙ በነበረበት ወቅት ማንም ሰው ማምለጥ በማይችል መልኩ በሁሉም አቅጣጫ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች እየተከታተሉ የግድያና የጭፍጨፋ ተግባር ይፈጽሙ እንደነበር ተገልጿል። በማይካድራ ከተማ በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸመው ጭፍጨፋ ተራ ወንጀል ሳይሆን የታቀደ እና በጥንቃቄ ተቀነባብሮ የተፈጸመ እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።        

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በስለት ተወግተው ወይም ተቀጥቅጠው እንደተገደሉ ማረጋገጡን አመልክቷል። “ወደ ከተማው ስንገባ ያየነው ነገር እጅግ አሳዛኝ ነበር፤ መንገዶቹ በተለይ የከተማው መሃል በሬሳዎች ተጥለቅልቀዋል” በማለት የአይን እማኞች እንደገለጹለት የዘገበው አምነስቲ ኢንተርናሽናል አመልክቷል።

አሸባሪው ህወሓት በማይካድራ የፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ በዓለም አቀፍ ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ ስለመሆኑ በርካታ የህግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ሌሊቱን ሙሉ የተፈጸመው ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፣ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸመ ከባድ የጭፍጨፋ ወንጀል መሆኑን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት ያስረዳል።

ድርጊቱ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime) ሊሆን እንደሚችልም ሪፖርቱ አመላክቷል። የሚያሳዝነው ነገር ይህ ከፍተኛ በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል “የመብት ተሟጋች ነን” የሚሉ ምእራባውያን ተቋማት እና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው አይተው እንዳላዩ በዝምታ ማለፋቸው ነው።

አሸባሪው ህወሓት በማይካድራ ጭፍጨፋ ከመፈጸሙ በፊት ጥቃት የሰነዘረው በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ነበር። ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝን ከምሽቱ 4 ሰዓት ጀምሮ ከውጭ በትግራይ ልዩ ሃይል በማስከበብ ከውስጥ የአሸባሪው ሃይል ተኩስ ከፍተው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ፈጽመዋል። የአሸባሪው ህወሓት አመራሮች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ እንደምትበታተን ሲዝቱ የቆዩ ሲሆን ይህን እኩይ ዓላማቸው እውን ለማድረግ ሲሉ ነበር በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ያበቃቸው።  ይሁን እንጂ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምኞታቸውን በማክሸፍ በጀግንነት ሊወጣው ችሏል።   ይህ የሽብር ቡድን ሀገር የማፍረስ ህልሙ አሁንም ሊያቆም አልወደደም። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ትንኮሳዎችን በመፍጠር መረጋጋት እንዳይኖር እየሰራ ይገኛል።

ማይካድራ ላይ ጭፍጨፋ የፈጸመው የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች እና ሳምሪ የተባሉ ወጣቶች ድርጊቱን ከፈጸሙ በኋላ በስደተኛ መልክ ወዲያው ያቀኑት ወደ ሱዳን ነበር። ወንጀል ፈፃሚው የአሸባሪው ህወሓት አባላት ከተፈናቃዮች ጋር ተቀላቅለው እርዳታ ሲቀበሉ ለወራት ከመቆየታቸውም በላይ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የተዛባ ምስል እንዲይዝ በማድረግ ሴራ ሲሸርቡ ቆይተዋል። እነዚህ አካላት ከወራት ቆይታ በኋላ በድጋሚ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ተዘጋጅተው በሁመራ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር ይታወሳል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የሃይል ስምሪት ሃላፊ ብርጋዴል ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ያለፈው ግንቦት ወር ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ወደ ሱዳን የተሰደዱት ጨፍጫፊዎች ለወራት አሜሪካና ሱዳን ከሚገኙ የአሸባሪው አባላት በሚደረግ ድጋፍ ስልጠና ሲወስዱ ቆይተው በተደጋጋሚ ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ሙከራ ቢያደርጉም በመከላከያ ሰራዊቱ እንደከሸፈባቸው ገልጸዋል። ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላም 320 የሚሆኑት በሃምዳይት ሁመራ በኩል ትጥቅና የተለያዩ መድሃኒቶችን ይዘው ለመግባት ሲሞክሩ አብዛኛዎቹ በመከላከያ ሰራዊቱ ሲደመሰሱ ቀሪዎቹ መማረካቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ሲፈጽም ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም በማይካድራ የተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ ግን በዓይነቱ ልዩ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ቡድን ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን የመምራት ስልጣን ባገኘበት ወቅት በዜጎች ላይ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ሲፈጽም እንደነበር የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በየዓመቱ ሲያወጧቸው የነበሩ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። አሸባሪው ህወሓት ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በመገደብ፣ የተለየ ሀሳብና አቋም የሚይዝ ማንኛውም አካል በሽብርተኝነት በመፈረጅ ለእስርና እንግልት ሲዳርግ እንደነበር የችግሩ ሰለባዎች በዝርዝር ያስረዳሉ።

“ጂኖሳይድ ዎች” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት እ.አ.አ ጁላይ 2020 ባወጣው ሪፖርቱ ላይ በቀድሞው የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ህወሓት ሀገሪቱን በአድራጊ ፈጣሪነት ሲያስተዳድር እንደነበር ጠቁሞ፤ እ.አ.አ በ2003 በጋምቤላ ክልል በአኙዋክ ላይ እንዲሁም በሶማሌ ክልል በኦጋዴን የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን አመልክቷል። ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ድርጅት በየዓመቱ ሲያወጣቸው በነበሩ ሪፖርቶች በሀገሪቱ ሲፈጸሙ የነበሩ ኢሰብአዊ ድርጊቶች ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል። ለአብነት በ2016 ሪፖርቱ ላይ  የፀጥታ ሃይሎች ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ህጻናትን ጨምሮ እስረኞችን በፕላስቲክ ቆመጥ እና አለንጋ መደብደብ፣ ብዙዎች እጃቸው ወደ ኋላ በማሰር አንጠልጥሎ መግረፍ፣ በኤሌክትሪክ በማንዘር ማሰቃየት፣ እንዲሁም ሴት ታሳሪዎች ሲደፈሩ እንደነበር ይፋ አድርጓል። የፀጥታ ሃይሎች ግለሰቦችን ይዘው ይሰውሯቸው እንደነበር የሂዩማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ያሳያል።፡

አሸባሪው ህወሓት አሁንም ህፃናትን እየመለመለ ለጦርነት በማሰለፍ ተጨማሪ ጥፋት እየፈጸመ ይገኛል። በቅርቡ ለመከላከያ ሰራዊት እጃቸውን የሰጡ ህፃናት እንደገለጹት አደንዛዥ እጽ በመስጠት በርካታ ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ እየማገዳቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል። ህፃናትን ለጦርነት ማሰማራት ከፍተኛ የስነ ልቦና ችግር የሚያስከትል ከመሆኑም በላይ በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚያስጠይቅ ስለመሆኑ የህግ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የሽብር ቡድኑ የፈጸማቸውና እየፈጸማቸው የሚገኙ ድርጊቶች በዓለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቀው ስለመሆኑ ተግባራቱ ግልጽ ማሳያዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም