ቀጥታ፡

በመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ልዩ ዘጋቢ ላወጣው የተሳሳተ መግለጫ ኤጀንሲው ምላሽ ሰጠ

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ልዩ ዘጋቢ የኤርትራ ስደተኞችን በሚመለከት ላወጣው የተሳሳተ መግለጫ የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ምላሽ ሰጠ።

በመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ስፔሻል ራፖርተር በዶክተር ሞሀመድ አብዱሰላም ከሱዳን የወጣው መግለጫ ፍፁም የተሳሳተና የኢትዮጵያን ሚና ዝቅ ያደረገ መሆኑን ገልጿል።

መግለጫው ፍፁም የተሳሳተ፣ ፈጠራ እና እውነታነት የሌለው እንዲሁም ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ያላትን መልካም ስም የሚያጎድፍ መሆኑን ኤጀንሲው በመግለጫው ጠቅሷል።

መግለጫው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የፈፀመውን እኩይ አላማና የወንጀል ድርጊት ከኢትዮጵያ መንግስት መልካም እንቅስቃሴ ለይቶ ያልተመለከተ መሆኑንም ጠቁሟል።


የወጣው መረጃ እውነታ የጎደለው፣ የተዛቡ መረጃዎች የተካተቱበት፣ የፈጠራና በተጨባጭ ያሉ እውነተኛ መረጃዎችን ያላካተተ መሆኑን ኤጀንሲው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኞች አሁን ካሉበት አስጊ አካባቢ ለማዘዋወር እያደረገ ላላው ጥረት እውቅና ያልሰጠና የአሸባሪውን ህወሃት እኩይ ተግባር ያላጋለጠ መሆኑንም ጠቅሷል።

መግለጫው አሸባሪው ህውሃት በመጠለያ ጣቢያዎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ግድያ፣ ጠለፋ፣ ዝርፊያና በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከባድ መሳሪያ አጥምዶ ሽብር ሲፈጠር አይቶ እንዳላየ ማለፉንም አውስቷል።

መንግስት ስደተኞችን ለመንከባከብ ብዙ ጥረት ያደረገ ሲሆን በርካታ ስደተኞችን ከነበሩበት አስቸጋሪ ስፍራ በማስወጣት ወደተሻለ ስፍራ ማዛወሩን አስታውሷል የኤጀንሲው ምላሽ።

መንግስት የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ቢያሳልፍም አሸባሪው በእኩይ ተግባሩ ቀጥሏልም ብሏል።

በመሆኑም የወጣው መግለጫ የኢትዮጵያን መንግስት ጥረትና ልፋት የካደ፣ እውነታ የሌለው የፈጠራ ወሬ ሲል ኤጀንሲው አጣጥሎታል።

ኤጀንሲው በምላሹ ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምታደርገውን ድጋፍና እገዛ አጠናክራ ትቀጥላለች ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለውን ያላሰለሰ ጥረት የተባባሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ እነዲያደርጉ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም