ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ተመለከተ
ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 1/2013(ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍና ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው ተመለከተ።
የግድቡን አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች እንዲሁም ጂኦ ፖለቲካዊ አንድምታዎች በኢትዮጵያና በናይል ተፋሰስ አካባቢዎች በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በድሬዳዋ የፓናል ውይይት ተካሄዷል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ግድቡ ከተረጂነት የሚያወጣንና ወደ ከፍታ ከሚያሻግሩን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ዋነኛው ነው፡፡
በዚህም በራስ አቅም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር ለመገንባት የሚካሄዱ ሥራዎች ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ባለፈው ወር የተካሄደው የግድቡ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ወሳኝ እንደነበር ምክትል ከንቲባው አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሚገባትን ቦታና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን የሚያረጋግጠውን የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የፓናል ውይይቱ በዲፕሎማሲው መስክም ምሁራኑ እያከናወኑ የሚገኙትን በድል የታጀቡ ተግባራትና አበረታች ሥራዎች ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
የሣይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው፤ ግድቡ የኢትዮጵያን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብትና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ትርጉም ባለው መንገድ የሚለውጥና ከፍታ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ከአባይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በጥልቅ እውቀት፣ ክትትልና በአሳታፊነት ለመምራት ከውጭ ጉዳይ፣ ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴሮች ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ይህን የሀገር ታላቅነትና የብልጽግናና ማረጋገጫ የሆነውን ግድብ ለማጠናቀቅ ዜጎችና ምሁራን ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
በተለይም ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት በአባይ ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ፣ ፖለቲካዊና የሥነ-ምህዳር ጉዳዮች ላይ ምርምሮች በማካሄድ መፍትሄዎች ለማበጀትና ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ላይ ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል፡፡
በዚህም በወንዙና ተፋሰሱ ዙሪያ የሚገኙ አስር ዩኒቨርሲቲዎች ወንዙን ከደለል ለመታደግ የጀመሯቸውን ጥናቶች በመልካምነት አንስተዋል፡፡
''ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መልካም ተፅዕኖ ከግድቡ በላይ ነው፤ ግድቡ ሉአላዊነት፤ ፍትሃዊነት፣ አንድነትና ብሔራዊ መልዕክት ነው'' ያሉት ደግሞ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሣትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ናቸው ፡፡
''የአድዋ ድል አፍሪካን የፖለቲካ ነፃነት እንዳጎናጸፈ ሁሉ፤ ግድቡ ደግሞ የኢኮኖሚ ነጻነት ያጎናጽፋል'' ይላሉ፡፡
ግድቡ ከብድርና እርዳታ ተፅዕኖ የሚገላግል ፍቱን መድኃኒት፣ የሀገሪቱን የብልጽግናና በራስ ሃብት ማደግ እንደምትችል ማሳያ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም መብቷን ዳር ለማድረስ የጀመረችው ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ምሁራንም በምርምርና ጥናት፣ በዕውቀትና ክህሎት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መስራት ይገባናል ነው ያሉት፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ ምሁራንና አምባሳደሮች በግድቡ ሁለንተናዊ ጥቅሞች፣ በአባይና በአባይ ተፋሰስ የውሃ ሃብት ጥቅሞችና ተግዳሮቶች፣ ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ ጉዳዮች እንዲሁም በተፋሰሱ ውስጥ በሚኖሩ ህዝቦች ጉዳይ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፎች አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡