የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመስጠት ቃል ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመስጠት ቃል ገቡ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 1/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመስጠት ቃል ገቡ።
የኮርፖሬሽኑ ዘጠኝ ሰራተኞችም ሰራዊቱን ለመቀላቀል ተዘጋጅተዋል።
የህወሃት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች የአገራቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ግንባር ላይ ይገኛሉ።
በመሆኑም ለአገሩ ክብርና ሉአላዊነት እየተፋለመ ለሚገኘው ሰራዊት የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን አመራርና ሰራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
አመራርና ሰራተኞቹ ከገንዘብ ድጋፉ በተጨማሪ ደማቸውን ለሰራዊቱ በዛሬው እለት ለግሰዋል።
የአገራችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚደረገውን ርብርብ በምንችለው ሁሉ እንደግፋለን ሲሉም አረጋግጠዋል።
የኮርፖሬሽኑ ሰራተኛ ወጣት መለሰ ግዛቸው የወር ደሞዙንና ደሙን ከመለገሱ በተጨማሪ ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀቱን ገልጿል።
''እኛ የምንኖረው አገር ስትኖር ነው'' ያለው ወጣቱ እኔም ከሰራዊቱ ጋር ተቀላቅዬ አሸባሪውን ለመደምሰስ ተዘጋጅቻለሁ ብሏል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብም በገንዘቡና በጉልበቱ አገሩን ለማዳን እንዲነሳ መለሰ ጠይቋል።
"ሁሌም ከሰራዊቱ ጎን እንቆማለን፤ ሁሉም በሚችለው ሰራዊቱን ለማገዝና አሸባሪውን ለመዋጋት ተዘጋጅቷል" ብለዋል ሰራተኞቹ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ ሰራተኞቹ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ለመስጠትና በተከታታይም ደም ለመለገስ መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ሰራተኞቹ በሙሉ ፍቃደኝነት በራሳቸው ተነሳሽነት የሚፈለገውን ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናቸውም ብለዋል።
የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ከዚህም ቀደም ለሰራዊቱ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መቆየቱን ገልጸው አሁን የተቋሙን መጋዘኖችና ተሽከርካሪዎች ለሰራዊቱ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።