ቀጥታ፡

የህወሃት አሽባሪ ቡድን እያደረሰ ያለውን ሰብአዊ ቀውስና ውድመት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዝና ጫና ሊያደርግበት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) የህወሃት አሽባሪ ቡድን እያደረሰ ያለውን ሰብአዊ ቀውስና የሃብት ውድመት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዝና ጫና ሊያሳድርበት እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊነትን ማዕከል በማድርግና የትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ በሚል የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉ ይታወቃል።

ይሁንና አሸባሪው ሕወሓት የተናጥል የተኩስ አቁሙ ማግስት ጀምሮ በአማራና አፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ጦርነት በመክፈት ሰብአዊ ቀወስና የንብረት ውድመት እያስከተለ ይገኛል።

ቡድኑ ሰሞኑንም በአፋር ክልል የእህል መጋዘንን ያወደመ ሲሆን በአማራ ክልል ደግሞ ታሪካዊና ኃይማኖታዊ ቅርሶችን የማውደም እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ ተመልክቷል።

ከዚህም አልፎ ወደ 300 ሺህ ዜጎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለተጨማሪ ችግር እንዲዳረጉ ምክንያት መሆኑም ነው የተገለጸው።

በመሆኑም የአሸባሪ ቡድኑ ሕገ-ወጥ ተግባራት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቅጡ እንዲረዳውና እንዲያወግዘው እንዲሁም ከፍተኛ ጫና ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።

የአገሪቱን ሉአላዊነትና አገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ መንግስት የመከላከል አቅሙን ለመጠቀም የሚገደድ መሆኑን ትላንት ባወጣው በመግለጫ ተመልክቷል።

ኢዜአ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ የአፍሪካ የአመራር ልህቀት ማዕከል መምህርና ተመራማሪ ከዶክተር ዳኒኤል ኤባና ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የፖለቲካ ምሁሩ ዶክተር ንጉሴ በላይ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የፌዴራል መንግሥት ችግሮች በተሻለ መልኩ እንዲፈቱ ለማድረግ ጥረት ቢያደርግም በአሸባሪው ሕወሓት ልፋቱ በከንቱ መቅረቱን ዶክተር ዳኒኤል ገልጸዋል።

ቡድኑ መንግሥት ላደረገው ተኩስ አቁም ተገቢ ምላሽ ቢሰጥ ኖሮ ሰብዓዊ ቀውሱን ማስቀረት ይቻል ነበር ይላሉ።

የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ሁኔታ የተረዳበት መንገድ ችግር እንዳለበት ገልጸው አንድ ወገን ላይ የተንጠለጠለ ነውም ብለዋል።

የተወሰኑ ሃይሎች የኢትዮጵያን እውነታ ማመን ባይፈልጉም አብዛኞቹ ግን ትክክለኛ መረጃ ካገኙ ከኢትዮጵያ ጎን ይሰለፋሉ ብለዋል።

የአገር ህልውናና አንድነት እንዲጠበቅ አሸባሪው ቡድን ፈቅዶና ወዶ ወደ ሰላማዊ መንገድ ካልመጣ በቀጣይ ተገቢና የተጠናከረ እርምጃ ያስፈልጋል ነው ያሉት ዶክተር ዳኒኤል።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የፖለቲካ ምሁሩ ዶክተር ንጉሴ በላይ በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ በአዋሳኝ ክልሎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር የእርዳታ አቅርቦትን በማስተጓጎል ሰብአዊ ቀውስ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በርካታ ንጹሃን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳያገኙ በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አደጋ ላይ እንዲወደቁ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት። 

ቡድኑ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅባቸውን ቅርሶች ላይም ጭምር አደጋ እንዲደቀን በማድረግ የአገርን ሉዓላዊነት ተፈታትኗል ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ የመንግሥትን የተናጠል የተኩስ አቁም ባለመቀበል በአጎራባች ክልሎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት አለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያየ በዝምታ ማለፉ በርካቶችን አስገርሟል ብለዋል። 

በመሆኑም በዚህ አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ባለው የሽበር ቡድን ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም