ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚገዳደረውን ሃይል ለመፋለም ተዘጋጅተናል- የካፋ ዞን ነዋሪዎች

አበባ አበባ፣  ነሃሴ 01/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚገዳደረውን ሃይል ለመፋለም መዘጋጀታቸውን በደቡብ ክልል የካፋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተዋልደውና ተከባብረው የሚኖሩባት አገር ብትሆንም ይህን የህዝቦች አብሮነትና አንድነት ለመናድ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ሃይሎች ሙከራ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት የሚገዳደርን ማንኛውንም ሃይል ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይ ተሰማ ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫና ሁለተኛ ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትን በስኬት በማጠናቀቅ ታላቅነቷን ለዓለም አሳይታለች ብለዋል።

እንዲህ ዓይነት ድሎች በህዝቦች የተባበረ ክንድና በአገራዊ መግባባት የሚመጡ መሆናቸውን ጠቅሰው ካፋን ጨምሮ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሩ ጉዳይ የሚመጣን አደጋ በጋራ ይመክታል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ በባህል፣ በቋንቋና በአኗኗር ዘይቤ ያለውን ልዩነት ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ብቻ ወደ ጠብና ጥላቻ እንዲለወጥ የፖለቲካ ሴራ ሲሰራ ነበር ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ይህን ሴራ በተባበረ ክንድ በማክሸፍ አገራቸውን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን በጋራ መስራት ጀምረዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በመከባበርና በአንድነት የትኛውንም ጠላት የማሸነፍ ሃይል አላቸው ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም