ቀጥታ፡

በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ሠላማዊ ሠልፍ ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) የህወሃት አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማውገዝ ለአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የፀጥታ አካላት የድጋፍ ሰልፍ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ ነዋሪዎች በነገው ዕለት በመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ ያደርጋሉ፡፡

የነገውን የድጋፍ ሰልፍ አስመልክቶ ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን መኖራቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።

በሰላማዊ ሰልፉ በሺዎች የሚቆጠሩ ፈረሰኞችም ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ነዋሪዎቹ ለፀጥታ ሃይሉ ደጀን መሆናቸውን ለማሳየት የሚያደርጉት መሆኑን ነው መግለጫው ያመላከተው።

የአዲስ አበባ የድጋፍ ሰልፍ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን ፖሊስ ኮሚሽኑ ገልጿል።

ለሰላማዊ ሰልፉ የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውንና በዕለቱ ለትራፊክ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን ፖሊስ ገልጿል።

በዕለቱ በመስቀል አደባባይ የሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ የተወሰኑ መንገዶች ለጊዜዉ ለትራፊክ ዝግ ይሆናሉ፡፡

በዚህም መሰረት፦

•  ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ  ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር ኦሎፒያ አደባባይ

•  ከመገናኛ ፣ በሃያ ሁለት ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድሃኔዓለም፣ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል   አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ

•  ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ  ባሻወልዴ ችሎት ወይም ፓርላማ መብራት

•  ከቸርችል ጎዳና ወደ መስቀል አደባባይ  የሚወስደው መንገድ ቴዎድሮስ አደባባይ እና አገር አስተዳደር መብራት ወይም ኢሚግሬሽን

•  ከተክለ ሀይማኖት በሜትሮሎጂ መስቀል አደባባይ  የሚወስደው መንገድ ሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት አካባቢ

•  ከተክለ ሀይማኖት ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ኢሚግሬሽን ጥቁር አንበሳ የኋላ በር

•  ከጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ፣ ብሄራዊ ቲያትር የሚወስደው መንገድ ጎማ ቁጠባ

•  ከሳሪስ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ  የሚወስደው መንገድ አጎና ሲኒማ  እና አራተኛ ክፍለ ጦር

•  ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ሜክሲኮ አደባባይ

•  ከጦር ኃይሎች ወደ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ፣ ሜክሲኮ፣ ለገሀር  የሚወስደው መንገድ ለገሃር መብራት  አካባቢ   ለተሽከርካሪ ዝግ ይሆናሉ።

በተጨማሪም ከዋዜማው ምሽት ጀምሮ ሥነ-ሥርዓቱ በሚከናወንበትና ዝግ በሚሆኑ መንገዶች አካባቢ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓት ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑ ተገልጿል።

ስለዚህም አሽከርካሪዎች ተገንዝበው አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ፖሊስ አሳስቧል።

በድጋፍ ሰልፍ ላይ ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ እንደሚኖር የፕሮግራሙ ተሳታፊዎች ተገንዝበው ለፍተሻ እንዲተባበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ጥሪውን አስተላልፏል።

ኅብረተሰቡ ጥቆማ ለመስጠት ወይም የፖሊስ አገልግሎትን ማግኘት ሲፈልግ በ011-1-11-01-11 ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 እንዲሁም በፌደራል ፖሊስ ስልክ ቁጥሮች 011-5- 52-63-03 እና በነፃ የስልክ ጥሪ 987 መጠቀም እንደሚችል አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም