ጀግኖች አባቶቻችን ያስረከቡንን ሀገር በአሸባሪው የትህነግ ቡድን አናስደፍርም!

ጅማ/አምቦ ነሐሴ 01/2013(ኢዜአ) ጀግኖች አባቶቻችን ያስረከቡንን ሀገር በአሸባሪው የትህነግ ቡድን አናስደፍርም ሲሉ ዘማች ወጣቶች አስታወቁ።

ከጅማና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች በራሳቸው ተነሳሽነት ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ለመሰለፍ የተዘጋጁ 1ሺህ 995 ወጣቶች  ወደ ማሰልጠኛ ተንቀሳቅሰዋል።

ወጣት ፎአድ ቃሲም  ከጅማ ዞን ወደ ማሰልጠኛ ከተንቀሳቀሱት መካከል አንዱ ሲሆን የአሸባሪውን ርዝራዥ ለማስወገድ በሚካሄደው ትግል ለመሳተፍ  በቁርጠኝነት መነሳሳቱን ለኢዜአ ተናግሯል። 


"ከሀገር በላይ ምንም ስለሌለ ለሀገሬ ቀን ከሌት ታግዬ ጽንፈኛውን ሀይል ከወንድሞቼ ጋር በመሆን ልደመስሰው ተዘጋጅቻለሁ" ብሏል።


ወጣቱ ቤት ንብረቱን ትቶ የሚዘምተው ጀግኖች አባቶቻችን ያስረከቡንን ሀገር በአሸባሪው የትህነግ ቡድን አናስደፍርም በሚል ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜትና ወኔ ተነሳስቶ ነው።


ሌላው ዘማች አቡሽ ከበደ በበኩሉ "እናት ኢትዮጵያዬን ማንም ሲደፍራት ማየት አልችልም፣ አሸባሪውን ትህነግ ከሀገር መከላከያ ጎን በመሰለፍ በግንባር እፋለመዋለው" ነው ያለው።


ወጣቶች በአንድነት ሆነን ሀገር የገጠማትን ጠላት ማጥፋት ይጠበቅብናል ሲል አመልክቷል።


ወጣቶች  ወደ ማሰልጠኛ ሲንቀሳቀሱ በሽኝት ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም  ሙሉ፤  እናንተ ጀግኖቻችን አሸባሪውን ቀብራችሁት እንደምትመለሱ እንተማመናለን ሲሉ ነው የገለጹት።


በሀገር ፍቅር ወኔ ተነሳስታችሁ  ጀግናውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለመቀላቀል ለወሰናችሁ ወጣቶቻችን ድል ይቀናችኋል ፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ብለዋል።
በተመሳሳይ ከምዕራብ ሸዋ ዞን 22  ወረዳዎች የተውጣጡ ዘማች ወጣቶች በፍላጎታቸው መከላከያን ለመቀላቀል ወደ ማሰልጠኛ ማዕከል ተንቀሳቅሰዋል።


ዘማች ወጣቶቹ ጀግኖች አባቶቻችን ያስረከቡንን ሀገራችን አናስደፍርም! ሲሉ በላቀ የሀገር ፍቅር ስሜት ድምጻቸውን በጋራ አሰምተዋል።

ከወጣቶቹ መካከል  ገረሙ ባልቻ በሰጠው አሰተያየት፤  ከሀገር መከላከያ ጎን በመሰለፍ የዜግነቱን  ለመወጣት በራሱ ተነሳሽነት መወሰኑን ተናግሯል፡፡

“የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው ማንኛውም ሀገራዊ ጥሪ ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን ነን ያለው ደግሞ  ወጣት ዳዊት ቶለሳ ነው፡፡

ወጣቶቹን መርቀው የሸኙት የሀገር ሽማግሌ አቶ በቀለ ሞሲሳ ፤ወጣቶቹ መንግስት ያቀረበላቸውን ጥሪ ምላሽ በመስጠት ጀግናውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለመቀላቀል በመወሰናቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ከአሸባሪው የትህነግ ርዝራዥ ሀገራቸውን ለመታደግ ለዘመቻው የተዘጋጃችሁ ሁላችሁም ጀግኖች ናችሁ  ሲሉም አስታውቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት  ጽህፈት ቤት የምዕራብ ሸዋ ዞን ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎሶምሳ ፤ ወጣቶቹ ሀገርን በማዳን ዘመቻ መሳተፋቸው እንኮራባቸዋለን ብለዋል፡፡

የትህነግ  ቡድን ሀገርን ለማፍረስ የሚያከናውነው የሽብር ተግባር መቼም ቢሆን እንደማይሳካ ተናግረዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን የጸጥታና አስተዳዳር ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኩምሳ ሂርጰሳ ዘማቾቹን አበረታትዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም