በሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ የምናስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የለንም - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ የምናስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የለንም
ነሐሴ 1/2013 (ኢዜአ)በሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ የምናስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የለንም ሲሉ የመቱ ከተማና የኢሉባቦር ዞን ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ ገለፁ።
የመቱ ከተማና የዞኑ ነዋሪዎች በሀገራችን ላይ እየተደረገ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነትንና የውስጥ ኃይሎችን ሀገርን የማፍረስ ሴራ የሚቃወም ሰልፍ ዛሬ በኢሉባቦር ዞን መቱ ከተማ እየተካሔደ ነው።
ከሁሉም የዞኑ ወረዳዎች የመጡ ሰልፈኞች በተሳተፉበት በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ሕዝቡ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለውን ድጋፍም አሳይቷል።
''የጀግንነት እንጂ የባንዳነት ታሪክ የለንም! የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ አንድነት ጋሻ ነው! በሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ የምናስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የለንም! የሚሉና ሌሎች መፈክሮች በሰልፉ ላይ ተስተጋብተዋል።
የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩ ነጋሽ በዚሁ ወቅት እንዳሉት አሸባሪው ሀይል አገር ለማፍረስ የወጠነው ሴራ አልተሳካለትም፣ ወደፊትም አይሳካለትም።
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም የውጭ ጣልቃገብነትን በመቃወምና በመታገል ''የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ እውን እናደርጋለን፣ አገራችንን በጋራ እንገነባለን'' ብለዋል።
የመቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ ጀምበሬ በበኩላቸው ሁላችን ከተባበርንና አንድ ሆነን ከቆምን የበለፀገች አገር ከመገንባት የሚያቆመን ሀይል እንደማይኖር ተናግረዋል።
አሸባሪውን ሀይል ለመደምሰስ የተጀመረውን ዘመቻ በድል ለማጠናቀቅ ሁሉም በአቅሙ ከመከላከያ ጎን መቆም እንዳለበትና የተጀመረው ድጋፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።