ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በማንኛውም ዕድሜና ሁኔታ ማገልገል ይገባል

ሀምሌ 30/2021 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በማንኛውም ሁኔታና ዕድሜ ውስጥ ሆኖ ማገዕልገል እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

በቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የተመሰረተው "ሴንተር ፎር ኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ኢትዮጵያ" የተሰኘ ድርጅት የማስተዋወቅና በዶክተር ሙላቱ የሕይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን "ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ከ1994 ዓ.ም እስከ....." የተሰኘ መጽሃፍ ምረቃ ተከናውኗል።

ሴንተር ፎር ኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለውን የኢንቨስትመንት ተግባር ለማገዝ መቋቋሙ ተገልጿል።

የድርጅቱ መስራች ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንደገለጹት የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ ሙያዊ አሻራ ለማሳረፍ ድርጅቱን ማቋቋም እንዳስፈለገ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ከዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የምጣኔ ሃብት ትስስር ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል በመንግስትና በባለሃብቶች መካከል ድልድይ ሆኖ ሙያዊና ስልታዊ ድጋፍ መስጠት የሚያስችል አገር በቀል ድርጅት እንደሚያስፈልግ በመገንዘብም እንደሆነ ገልጸዋል።

ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ኢንቨስትመንቶች እንዲጎለብቱ፣ ቀጣይነት እንዲኖራቸውና ለኢንዱስትሪያላይዜሽን አስተዋጽኦ ለማድረግም እንዲሁ።

ይህም የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማት፣ የሕዝቦቿን እድገትና ብልጽግና በተለይም የወጣቱን የስራ እድል ለማስፋት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋለ።

ድርጅቱ ድህነትን ለማጥፋት በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ራዕይና ተልዕኮም የሰነቀ  መሆኑን ዶክተር ሙላቱ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምህዳር እንዲሰፋ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ አማራጮችን በጥናትና ምርምር ምክረ ሃሳቦችን ለመንግስት በማመንጨት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዶክተር ሙላቱ ስራዎችና የሕይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው መጽሃፍ ታሪክን ለትውልድ ሰንዶ የማስተላለፍን ባሕል ለማዳበር ምሣሌ ይሆናል ብለዋል።

ዶክተር ሙላቱ "ሴንተር ፎር ኢንቨስትመንት ኔትወርኪንግ ኢትዮጵያ" የተሰኘውን ድርጅት ማቋቋማቸው በተለያዩ ዘርፎች ስራዎችን ለመንግስት ብቻ እንደማይተዉ ማሳያ እንደሆነም እንዲሁ።

የዶክተር ሙላቱ ተግባር አገርና ሕዝብን ማገልገል በስልጣን ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ዕድሜና ሁኔታ እንደሚቻል እንደሚያሳይም ነው ፕሬዚዳንቷ የተናገሩት።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የድርጅቱ መመስረት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ድርጅቱ ከተመሰረተ ጀምሮ ከኮሚሽኑ ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም እየሰራ እንደሆነና በቀጣይም ይኸው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

"ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ከ1994 ዓ.ም እስከ....." የተሰኘው መጽሃፍ ደራሲ አቶ አለምነህ ረጋሳ መፅሃፉ 440 ገጾች እንዳሉትና ይዘቱም ዶክተር ሙላቱ የሰሯቸውን ተግባራት የሚዳስስ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ህን ታሪክና ለኢትዮጵያ ያበረከቱትን መልካም ተሞክሮ ለትውልድ ማስተላለፍን ዓላማ አድርገው እንደጻፉትም ተናግረዋል።

ዶክተር ሙላቱ ተሾመም በአቶ አለምነህ ረጋሳ ተጽፎ ለአንባቢያን ስለበቃው መጽሃፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶችና እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም