ቀጥታ፡

ኤርትራዊያኑ ስደተኞች አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈፀመው ሕገወጥ ተግባር ለዘረፋና እንግልት ተዳርገዋል

ሃምሌ 30/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በፈፀመው ሕገወጥ ተግባር ለዘረፋና ለእንግልት መዳረጋቸውን ኤርትራዊያን ስደተኞች ተናገሩ።

ከትግራይ ክልል ሽመልባ ስደተኞች ካምፕ ተፈናቅለው አዲስ አበባ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ አስታውቋል።

ስደተኞቹ በአዲስ አበባ ለሶስት ወራት የሚኖሩበት ፈቃድ እንዲሰጣቸውና የተለያዩ ድጋፎች ማግኘት የሚያስችሏቸው ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹላቸው መሆኑንም ገልጿል።

ከስደተኞቹ መካከል ዶክተር ፍጹም ዚያድ ከ14 ዓመታት በፊት ከኤርትራ ተሰደው ወደ ሽመልባ የስደተኞች ካምፕ መግባታቸውን ይናገራሉ።

ነገር ግን በቅርቡ በትግራይ ክልል አሸባሪው የህወሓት ቡድን በስደተኞች ላይ አደጋ በመፍጠሩ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ገልጸዋል።የኩናማ ስደተኛ ነኝ ያሉት አቶ ዲግላል እንድሪያስም ግጭት ሲቀሰቀስ በሽመልባ ካምፓ የነበረው ስደተኛ ለከፋ ስቃይ፣ እንግልትና ድብደባ መዳረጉንና ጥቂት የማይባሉም ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ተናግረዋል።

እርሳቸውም ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ከሶስት ስደተኞች ጋር በመሆን ፈታኝ የእግር ጉዞ በማድረግ ጎንደር መግባታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ ለሶስት ወራት ድጋፍ እንድናገኝ ምዝገባ እያደረገልን መሆኑ አስደስቶናልም ብለዋል።

ግጭቱ ሲቀሰቀስ በሽመልባ ስደተኛ ካምፕ የነበሩ ልጆቻቸውን ለማውጣት ሶስት ቀን እንደተጓዙ የገለጹት ደግሞ አቶ እስራኤል ታምሩ ናቸው።

የልብ ሕመምተኛ ልጃቸውን ከካምፑ ለማውጣት በሚያደርጉት ጥረት በህወሓት የሽብር ቡድን እንግልትና ስቃይ እንደደረሰባቸው ነው የገለጹት።

የሽብር ቡድኑ የስደተኛ ካምፑን በመዝረፍ፣ ስደተኞችን በመደብደብና በማሰቃየት ስራ ተጠምዶ እንደነበር የዓይን እማኝ ነኝ ይላሉ።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ያሲን አሊ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሽመልባና ሕፃጽ ካምፖች የኤርትራ ስደተኞች ላይ ከፍያለ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

ስደተኞቹ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደተለያዩ አካባቢዎች በመበታተናቸው ኤጀንሲው እነሱን የማሰባሰብ ስራ እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

በዚህም አዲስ አበባ የሚገኙ ስደተኞች ድጋፍ እንዲያገኙ የምዝገባና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹላቸው ነው ብለዋል።

በስደተኞች ስም ድጋፉ የማይገባቸው እንዳይቀላቀሉ ቀደም ሲል የነበረውን ዳታ የመፈተሽና ትክክለኛነቱን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም