በመተከል ዞን የተከናወኑ የሠላም ማስፈን ተግባራት ስኬታማ ናቸው

47

ሐምሌ 30/2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ሠላምና መረጋጋት ለማስፈን የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን የዞኑ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ገለጹ።

በዞኑ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ከቡለን ወረዳ አካባቢ ነዋሪዎች ጋር ተወያይቷል።

የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት አሸባሪው የህወሓት ቡድን መተከልን የግጭት ቀጣና ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።

በዚህም የዜጎች ሕይወት እንዲጠፋና ከመኖሪያቸውም እንዲፈናቀሉ አድርጓል ብለዋል።

ዞኑ በኮማንድ ፖስት መመራት ከጀመረ ወዲህ ለማረጋጋት የተሰሩ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን የገለጹት ሌተናል ጄኔራሉ፤ አሁንም አልፎ አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን የመፍታት ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው ሠላም ለማምጣት ሠራዊቱ መስዋዕትነት መክፈሉንም ጠቅሰዋል።

በዞኑ የመንግስትን የሠላም ጥሪ የተቀበሉ ወጣቶችን በማሰልጠን የተሰሩ ስራዎችም አበረታችና ተሰፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም የአካባቢው ኅብረተሰብ አፍራሽ ተግባራት ላይ የተሰማሩትን ግለሰቦች ወሬ ባለመስማት ውስጣዊ አንድነቱን ማጠናከር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው እየተደረገ ያለው ሠብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች ተለይተው ለሕግ ይቅረቡ ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም