ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የመተንፈሻ ማገዣ /ኦክስጅን/ የማምረት አቅም በሠዓት አምስት ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ደርሷል

 ሐምሌ 30/2013(ኢዜአ)  የኢትዮጵያ የመተንፈሻ ማገዣ /ኦክስጅን/ የማምረት አቅም በሠዓት አምስት ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ መድረሱን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ ላለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጿል።

የሚኒስቴሩ የሕክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ያዕቆብ ሰማን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ የበሽታ ቅኝት ከማድረግ ባሻገር የሕክምና አገልግሎት ላይ እየሰራ ነው።

በዚህም የኦክስጅን የማምረት አቅምን በሠዓት ከነበረበት 2 ሺህ 400 ሜትሪክ ኪዩብ ወደ 5 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ማሳደግ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በፅኑ ሕክምና መድኃኒቶች አቅርቦትም 85 በመቶ ክምችት መያዙን ጠቅሰዋል።

የጤና ተቋማት ለኮቪድ-19 ሕክምና በቂ አልጋ እንዲያዘጋጁ እየተደረገ መሆኑንናስለ በሽታው ግንዛቤ የማሳደግ ተግባራትም እየተከናወኑ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ለወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጋለጡና ሊጎዱ እንዲሁም በሽታውን ሊያዛምቱ የሚችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተለይተው ክትባት እየተሰጣቸው እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን የገለጹት አቶ ያዕቆብ በበሽታው የመያዝ ምጣኔና በፅኑ ሕክምና ክፍል እየታከሙ ያሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ብለዋል።

ይህም አገሪቷ ካላት የፅኑ ሕሙማን አልጋ፣ ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ ማሽንና መድኃኒት አንፃር ፈታኝ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

አሁን ያለው ሁኔታ በኢትዮጵያ የወረርሽኙ ሦስተኛው ወጀብ ሊከሰት እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዴልታ የተሰኘው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አይነት በዓለም ብሎም በአፍሪካ አገራት መከሰት ከከዚህ ቀደሞቹ ወጀቦች የአሁኑን አሳሳቢ ሊያደርገው ይችላልም ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዴልታ የተሰኘው የኮቪድ-19 ዝርያ መኖሩን ለማረጋገጥ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ ያዕቆብ፤ ዝርያው እንዳለ በማሰብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የጤና ተቋማት፣ ኅብረተሰቡ እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ወረርሽኙ አጠቃላይ ምላሽ የሚፈልግ መሆኑን ተረድተው ጥንቃቄ እንዲያደርጉና የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም