ለአካል ጉዳተኞች መብት መከበር በእውቀት የተደገፈ የአካታችነት ስራ መስራት ይኖርበናል - አቶ ፍቃዱ ፀጋ - ኢዜአ አማርኛ
ለአካል ጉዳተኞች መብት መከበር በእውቀት የተደገፈ የአካታችነት ስራ መስራት ይኖርበናል - አቶ ፍቃዱ ፀጋ
አዳማ ፤ ሐምሌ 30/2013(ኢዜአ) የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ከማስከበር አንፃር በእውቀት የተደገፈ የአካታችነት ስራ መስራት ይኖርበናል ሲሉ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ምክትል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ተናገሩ።
የአካል ጉዳተኞችን አሳማኝና ብቁ የሆነ የፖሊሲ፣ የልማት ዕቅድና ስትራቴጅ፣ የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች አካታችነት ላይ ያተኮረ የህግ ባለሙያዎች መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።
አቶ ፍቃዱ ፀጋ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ያለ አካል ጉዳተኞች አሳማኝ ተሳትፎና አካታችነት የሀገር ልማትና እድገት አይረጋገጥም።
ስለ አካል ጉዳተኞች መስራት የችሮታ ሳይሆን የመብት ጉዳይ መሆኑን ሁላችንም ተገንዝበን አካታች የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች እንዲዘረጉ ማድረግ አለብን ብለዋል።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን የወጣውን ትልቁን የሰብዓዊ መብት ዶክመንት ማስከበርና ማክበር በህገ መንግስቱ የተሰጠን ሃላፊነት ከመወጣት አንፃር በመድረኩ መፈተሽ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ከማስከበር አንፃር በእውቀት የተደገፈ የአካታችነት ስራ መስራት ይኖርበናል ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ 110 ሚሊዮን ህዝብ ባላት ሀገር ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ምን ያህል እንደሆኑ ማሰብ አለብንም ሲሉ ነው የተናገሩት።
እንደ ተቋም ህግ በማርቀቅ፣ ነፃ የህግ አገልግሎት በመስጠት፣ዓለም አቀፍ ህጎችና ማዕቀፎች እንዲተገበሩ በማድረግ ረገድ የአካል ጉዳተኞችን መብት ማስከበር ላይ አሁንም ትኩረት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
መድረኩ የአካል ጉዳተኞችን ስራ በባለቤትነት ለመስራት የሚያስችለንን አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።
የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅማ ድልቦ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት የመንግስት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎችም ድርጅቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።
አካል ጉዳተኞች ምቹ የስራ ምህዳር እንዲያገኙ የህግ ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤና እውቀት ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።
የሚወጡ አዋጆች፣ደንቦችና መመሪያዎች አካል ጉዳተኞችን በትክክል ታሳቢ ያደረገ መሆን አለባቸው ያሉት አቶ ጅማ ፤ በኤጄንሲው የሚመዘገበው ማንኛውም ድርጅት ስለአካል ጉዳተኞች በስራ እንቅስቃሴው ውስጥ ማካተት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ውይዘሮ ወይንሸት ሙሉሰው እንዳሉት፤ አካል ጉዳተኞች በሀገሪቱ በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አካታች ፖሊስና ስትራቴጅ ከማዘጋጀት ጀምሮ አበረታች ጅምሮች አሉ።
ጅምሮቹን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም የአካል ጉዳተኞችን ያካተተ የህግ ማእቀፍ፣ አሰራርና የልማት እቅድ ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
አካል ጉዳተኞች እንደ ዜጋ የሀገሪቱ ህዝብ አካል በመሆናቸው ከማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፖለቲካዊ መስኮች ተጠቃሚና ተሳታፊ እንዲሆኑ ሁላችንም በቅንጅት መስራት አለብን ነው ያሉት።
ከለውጡ ወዲህ አካል ጉዳተኞች ተገቢውን ትኩረት ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ስራ አስኪያጀ አቶ አባይነህ ጉጆ ናቸው።
በተለይ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ የልማት ፖሊስዎችና የህግ ማዕቀፎችን እንዲኖሩ በመንግስት በኩል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ አካል ጉዳተኞች ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መደረጉን አውስተው፤ በምርጫው በህዝብ ተወካዮችና ክልል ምክር ቤቶች ከ60 በላይ ወንበር አካል ጉዳተኞች ማግኘታቸውንም አስታውቀዋል።
በመድረኩ ከፌደሬሽኑ፣ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ከሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ኤጄንሲና ከጠቅላይ አቃቤ ህግ የተወጣጡ የህግ ባለሙያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ የኢዜአ ሪፖርተር ከአዳማ ዘግቧል።