ቀጥታ፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለገሱ

አዲስ አበባ ሀምሌ 30/2013(ኢዜአ) የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለአገር መከላከያ ሠራዊት እና አሸባሪውን ህወሓት ለመደሰስ ለተሰለፉ የጸጥታ አካላት ደም ለገሱ።
በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የህልውና አደጋ የፈጠረውን አሸባሪው ህወሓትን በመዋጋት ላይ ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊትና  የጸጥታ ኃይሎች ደም የመለገስ ተግባር በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ይገኛል። ከነዚህ መካከል የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደም የመለገስ መርሃ ግብር ተጠቃሽ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች "አገር ስትኖር ነው እኛ የምንመኖረው። የአገር አንድነትን ለማስጠበቅ እየተዋደቀ ላለው የመከላከያ ሰራዊት ደም በመስጠታችን ደስተኛ ነን" በማለት መርህ ነው ደም የለገሱት።

በደም ልገሳው ከተሳተፉት ተማሪዎች መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት እንዳሉት፤ በምንም የማይተካ ህይወቱን ለሰጠ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት "የሚተካ ደም በመስጠታችን ደስተኛ" ናቸው።

የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ዳግማዊት በቀለ በሰጠችው አስተያየት፤ "ጥቂቶች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በአገር አንድነት ላይ እየጣሉ ያሉትን አካሄድ አወግዛለሁ" ብላለች።

"ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እቆማለሁ" ያለቸው ተማሪ ዳግማዊት፤ ጀግናው መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በመጠበቅ ሉዓላዊነታችን እንደያሚስከበር እምነቷ መሆኑን ገልጻለች።

ሌላዋ አስተያየቱዋን የሰጠችው ተማሪ ሳሮን አሰፋ እንደገለጸችው፤ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሰላም የሚያናጉ ሃይሎችን በመከላከልና አደብ በማስገዛት የአገሪቷን ሰላም ለሚያሰጠብቀው የመከላከያ ሠራዊት "ደም መስጠት ያንስበታል"።

"ከዚህ በፊት ደም ለሚያስፈልጋቸው እናቶችና ሌሎች ዜጎች ደም ስንለግስ ነበር። አሁን ደግሞ እኛን ለሚጠብቀን ሠራዊት ደም በመለገሴ ደስተኛ ነኝ" ብላለች።

የአገር ህልውናን ለማረጋገጥ ወጣቶች የአገር መከላከያን እየተቀላቀሉ ባሉበት ወቅት ደም መለገስ እጅግ ቀላሉ ነገር መሆኑን ነው የተናገረችው።

"አገርን ለማፍረስ የመጣውን ሃይል በአንድነት ተባብረን መከላከል አለብን። እኛ የምንኖረው አገር ስትኖር ነው" ብላለች።

"የእኛ መከላከያ ሰራዊት ከአገሩ አልፎ የአፍሪካን ሰላም እያረጋገጥ የሚገኝ ነው" ያለችው ተማሪ አቤኔዘር፤ ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጎን እንደምትቆም ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ደም ባንክ የሆሳዕና ቅርጫፍ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባሶሬ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ደም እየለገሰ ይገኛል።

በደም ባንኩ ቅርንጫፍ ከህብረተሰቡ ደም እየተሰበሰበ መሆኑን አመልክተው፤ ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተለይ የህልውና ዘመቻው በአሸባሪው ቡድኑ ላይ ከተጀመረ ወዲህ "ህብረተሰቡ በብዛት እየመጣ ደም እየለገሰ ይገኛል" ያሉት ሃላፊው፤  የህብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህልም እጨመረ መምጣቱን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም