ቀጥታ፡

ክልሉ የአሸባሪውን ርዝራዦች እያጸዳ ነው

አሶሳ ፤ ሐምሌ 30 / 20139(ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሸባሪውን ህወሃት ርዝራዦች ከአካባቢው እያጸዳ መሆኑ ተገለጸ ፡፡

የሽብር ቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ ለማክሸፍ የጸጥታ ሃይሉን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር እንዳመለከቱት፤  አሸባሪው ትህነግ  ከትግራይ ቀጥሎ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ሁለተኛ የጥፋት ግንባር አድርጎ ቆይቷል፡፡

አሁን ደግሞ ቡድኑ በሀገር ላይ የሚፈጸመውን የአፍራሽነት ሚና ለማስቀጠል በስውር ሲንቀሳቀስ እንደሚስተዋልም ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ላይ ያተኮረው ደግሞ የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ማደናቀፍን ዋነኛ ግቡ አድርጎ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ከአሸባሪው ቡድን ጀርባ የኢትዮጵያን መልማት የማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ኢስሃቅ፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተከታዮቹ የአሸባሪውን  የጥፋት ዕቅድ ለማስፈጸም ተባባሪ ሆነው እንደተሰለፉ አመላክተዋል፡፡

በመተከልና ካማሺ ዞኖች የተከሰቱ ግጭቶች ረጅም ጊዜ የወሰዱበት ዋነኛ ምስጢርም በክልሉ ብሎም በሀገር ላይ በተሸረበው ሴራ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

'' ህወሃት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ህዝብ በድሏል'' የሚሉት አቶ ይስሃቅ፣ ስልጣን ላይ በነበረበት 27 ዓመታት አባላቱን በማሰማራት በክልሉ ዘረፋ መፈፀሙን አወስተዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ስም በሰፋፊ እርሻ፣ በወርቅና ተፈጥሮ ሃብቶች ልማት ስም በመግባት ሕገ ወጥ ተግባራት መፈጸማቸውን በማሳያነት አመልክተዋል፡፡

ከለውጡ በኋላም ቡድኑ መቀሌ ቁጭ ብሎ በኢንቨስትመንት ስም ካመቻቻቸው  ግለሰቦች ጋር ግንኙነቱን በድብቅ እንደቀጠለ ጠቁመዋል፡፡

''አሸባሪው እድሜ ልኩን ስልጣን ላይ መቀመጥ ይፈልጋል'' ያሉት ሃላፊው፣ አሁንም የሀገሪቱን ሃብት በመዝረፍ ለግል ጥቅሙ ለማዋል ጉጉት እንዳለው  ነው የተናገሩት፡፡

በክልሉ የሽብርተኛውን ቡድን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በትግራይ ህዝብ ላይ የሚፈጸም በደል አስመስሎ ለማቅረብ እንደሚሞከር አመልክተው፤ የክልሉ ህብረተሰብ ፣ መንግሥትና ፓርቲ ግን ከህዝቡ ጋር ያለውን አብሮነት ማስቀጠል እንደሚፈልግ ግልጽ አድርገዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ከሌሎች እህትና ወንድም ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን የሽብርተኛውን ቡድን ርዝራዦች በማስወገድ ላይ  እንዲተባበሩም ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ ከለውጡ በፊት በቋሚነት የሚኖሩ ከሽብር ቡድኑ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው በተለይም ከለውጡ ወዲህ ከአካበቢው የሚሰወሩና ለረጂም ጊዜ ጠፍተው ከቆዩ በኋላ ድንገት ተመልሰው የሚመጡ ግለሰቦች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በግለሰቦቹ ላይ በተደረገው ክትትል የተገኘው መረጃ ግለሰቦቹ የሚንቀሳቀሱት ንግድን ሽፋን አድርገው መሆኑን ያመለክታል ብለዋል፡፡

ሽብርተኛ ቡድኑ በአዲስ አበባና ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዳደረገው ሁሉ በልማት ማህበር ስም በዘረፋ ያከማቸው የክልሉን ህዝብ መሬት፣ ንብረትና ገንዘብ እንዳለም ተናግረዋል፡፡

''በህገ-ወጥ መንገድ ከሕዝብ የተዘረፈ ሃብት ከሽብርተኛ እጅ መውጣት አለበት'' የሚሉት አቶ ኢስሃቅ፣ የቡድኑን የጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ መንገዶች ለመቆጣጠር ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ኢስሃቅ እንዳስታወቁት፤ በቅርቡም የቡድኑን ርዝራዦቹ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከክልሉ ለመክሰም አቅጣጫ ተቀምጦ የማጽዳት ስራ እየተካሄደ ይገኛል ፡፡

የሽብር ቡድኑ አሁንም ክልሉን የጥፋት ማዕከል ለማድረግ አቅዶ ቢንቀሳቀስም፤ ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመቀናጀት ግብዓተ መሬቱ እንደሚፈጸም እምነታቸው መሆኑን ነው  ያመለከቱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም