ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የኃይል ዘርፉን ይደግፋል

አዲስ አበባ ሃምሌ 30/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የኃይል ምንጮችን በማልማት የገጠሩን አካባቢ የኤሌክትሪክ ፍላጎት ማሟላት እንደሚያስችል ተገለጸ።

በተያዘው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ስድስት ቢሊዮን ችግኞች በመላ አገሪቷ እየተተከሉ ይገኛሉ።

የችግኞቹ መትከል ዓላማ ወንዞችን ከመድረቅና በደለል ከመሞላት በመከላከል የአየር ጠባይ ሚዛንን በመጠበቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ማጎልበትን ነው።  

በተለይም ትላልቅ ወንዞች ተገድበው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንዲችሉ ችግኝ መትከልና መንከባከብ ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሆነ ይታመናል።

ለዚህ ስኬት ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ የገጠር ኢነርጂ ልማት ማዕከል በዘርፉ ከተሰማሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር ዛሬ ችግኞችን ተክለዋል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል ገሰሰ አገሪቷ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የኃይል ዘርፉን እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከ80 በመቶ በላይ ሕዝቦች በገጠር በሚኖሩባት አገር የእንጨት ማገዶን መጠቀም የተለመደ ነው።

በመሆኑም ጥቅም ላይ የሚውሉ ደኖችን መልሶ መተካትና መንከባከብ ለነገ የሚባል ስራ አይደለም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ወንዞቿ የሚፈለግባቸውን ጥቅም እየሰጡ እንዳልሆነ ይታመናል ያሉት አቶ ሚካኤል ወንዞችን ከመድረቅና ከደለል ለመከላከል የኃይል ተጠቃሚነትን ለማስፋት የደን መመናመንን መከላከል ዋነኛ ተግባር መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

ማዕከሉና አጋር ድርጅቶቹ ከአምስት ሚሊዮን የሚልቁ ችግኞችን በመትከል ለመንከባከብ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

የኃይል ምንጮችን በማልማትና በማስፋፋት በገጠራማው የአገሪቷ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

"ቪታ" የተሰኘው የአየርላንድ የልማት ድርጅት ዳይሬክተር አቶ አስፋው መኩሪያ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ለማሳደግ ያግዛል።

የአየር ብክለትን ለመቆጣጠር፣ የኃይል ፍላጎትን ለመጨመር፣ ኢንቨስትመንት ለማስፋፋትና ለሌሎችም የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ የአየር ንብረት ብክለትን ከመከላከል ባሻገር በተለይ በልማት ወደኋላ በቀሩ አካባቢዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍም አክለዋል።

በኢትዮጵያ የንጹህ ማብሰያ ኅብረት ዳይሬክተር ወይዘሪት ቆንጂት ንጉሱ በበኩላቸው በገጠሩ አካባቢ ደኖች ለእንጨት ለከሰልና ለሌሎች አገልግሎቶች ስለሚውሉ ችግኞችን በመትከል መተካት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከዚህ ባሻገር የደን መመናመንን ለመከላከል ሌሎች ኃይል ቆጣቢ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ 20 ቢሊዮን ችግኞችን በአራት ዓመታት ለመትከል አቅዳ እየሰራች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም