ቀጥታ፡

ኢንሳ ሰራተኞቹ የተከሏቸውን ችግኞች የሚንከባከቡበት ሥርዓት ዘረጉ

አዲስ አበባ ሃምሌ 30/2013 (ኢዜአ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ሰራተኞች ከደመወዛቸው ገንዘብ በማዋጣት ችግኞችን የሚንከባከቡበት ሥርዓት ዘረጉ ።

የኤጀንሲው ሰራተኞች ባለፈው ዓመት የተከሏቸው ችግኞች ከ98 በመቶ በላይ መጽደቃቸውም ተገልጿል።

የኤጀንሲው አመራር አባላትና ሠራተኞች በጎሮ አይ.ሲ.ቲ ፓርክ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።  

በዚህም ከአንድ ሺህ በላይ የተቋሙን ሠራተኞች ያሳተፈው ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለምግብነት የሚውሉ እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሎሚና ዘይቱንን የመሳሰሉ የፍራፍሬ ችግኞች የተተከሉበት ነው።

በዛሬው መርሃ-ግብርም ሁለት ሺ ችግኞች ተተክለዋል።      

የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ሀብታሙ ተሾመ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፈው ዓመት  በአይ.ሲ.ቲ ፓርክ ውስጥ የተተከሉ አምስት ሺ ችግኞች ከ98 በመቶ በላይ ጸድቀዋል።   

ኤጀንሲው ችግኞችን ከመትከል ባሻገር በመንከባከብ ረገድ ለሌሎች ተቋማት አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።    

የተተከሉት ችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው እንዲጸድቁ ሠራተኛው ገንዘብ የሚያዋጣበት አሠራር ተዘርግቶ ወደ ተግባር መገባቱ ለተገኘው ውጤት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

በሰራተኞቹ የሚዋጣው ገንዘብ ተደራጅተው ችግኞችን ለሚንከባከቡ ወጣቶች ክፍያ እንደሚውል ተገልጿል።

  

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ፤ ሠራተኛው ኮሚቴ በማዋቀር በየወሩ ከ10 እስከ 500 ብር ድረስ እያዋጣ ችግኞችን ሲኮተኩት፣ ውሃ ሲያጠጣና የኮንፖስት ማዳበሪያ በመጠቀም እንክብካቤ ሲያደረግ ቆይቷል፤ ወደፊትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።  

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው "ዛሬ ያልዘራነውን ነገ ማጨድ አይቻልም፤ ለሚቀጥለው ትውልድ አሻራችንን በማሳረፍ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል" ብለዋል።

አገር የብዙ አሻራዎች ድምር ውጤት ነው፤ ለዚህም መሥራት ይገባናል ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያ ደመናን በመጠቀም ዝናብ ማግኘት የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ ሙከራ ማድረጓን አስታውሰው፤ ከሁሉም በላይ ግን ችግኞችን በመትከል በተፈጥሮ ዝናብ የተስተካከለ አየር እንዲኖር አረንጓዴ አሻራ የማሳረፉ ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።  

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉት ሠራተኞች መካከል አቶ ቴዎድሮስ አበበ በሰጡት አስተያየት፤ የአየር ንብረት ለውጡ የሚያስከትለው ጫና እየበረታ መምጣቱን አንስተው፤ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የመንከባከቡ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን አብራርተዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ በላይ በየነ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት ተቋሙ ባካሄደው የተለያዩ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሮች ላይ መሳተፋቸውን ገልጸው፤ "አረንጓዴ አሻራን ለማኖር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል" ብለዋል።    

በኢትዮጵያ በ2013 ዓ. ም. ክረምት ወራት ስድስት ቢሊዮን ችግኝ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመትከል የሚያስችል እቅድ ወጥቶ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወቃል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም