በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራ ተቀባይነት የለውም
አዲስ አበባ ሀምሌ 30/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ማብራሪያ ሰጠ።
የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላቱም የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ መረዳታቸውንና ለኢትዮጵያ አንድነትና ጥንካሬ መቆም እንደሚፈልጉ መግለፃቸው ተነግሯል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በመድረኩ ተገኝተዋል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ ሊቀ-መንበር ዶክተር ራሔል ባፌ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ማብራሪያ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረግ የአሉታዊ ጣልቃ ገብነት ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን እንጂ የሌላ አለመሆኑን ማስረዳታቸውን የገለጹት ዶክተሯ በዚህ ጉዳይ መንግስትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም እንደሚያራምዱ ማስታወቃቸውን ገልጸዋል፡፡
ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አገሪቷ ካለችበት ችግር በፍጥነት እንድትወጣ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወትና ለዚህም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም ምክር ቤቱ ጥሪ ማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ባከበር መልኩ በሠብዓዊ ድጋፍና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር መስራት የሚቻል መሆኑንም አብራርተናል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ከመጠበቅ አንጻር ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ግልጽ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ማብራሪያውን የተከታተሉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አባላትም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ መረዳታቸውንና ለአንድነትና ለጥንካሬዋ አብረን መቆም እንፈልጋልን ማለታቸውንም ዶክተር ራሔል ገልጸዋል፡፡
ሠብዓዊ ድጋፍን አስመልክቶም ከኢትዮጵያ ጋር መስራት የሚሹ መሆኑን መናገራቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለወከሏቸው አገራት እንዲያሳውቁና እውነታውን መግለጽ እንዲችሉ መግባባት ላይ መደረሱንም እንዲሁ፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ አባልና የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰይፈስላሴ አያሌውም በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ ርዕዮተ ዓለም ቢኖራቸውም በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት ጉዳይ አንድ አቋም እንዳላቸው ማስረዳት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ አባላትም ይህን ተረድተው ኢትዮጵያን በሚደግፍ መልኩ እንዲቆሙ ማስገንዘባቸውንም አክለዋል፡፡
በመድረኩ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ታድመዋል።