ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ተግባራትን ማከናወን አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ተግባራትን ማከናወን አለባቸው
አዲስ አበባ ሀምሌ 30/2013 (ኢዜአ) ዩኒቨርሲቲዎች ከውጭ አገራት ተቋማት ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ሥራዎችን ማከናወን እንዳለባቸው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉ ነጋ አስገነዘቡ፡፡
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የዩኒቨርሲቲዎች የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት ትናንት ተጠናቋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ከውጭ አገራት አቻ ተቋማት ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቀባቸው ዶክተር ሙሉ በውይይቱ ማጠቃለያ አመልክተዋል።
የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ያለውን እውነታ ማስረዳትና ጥቅሟን የሚያስጠብቁ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ዶክተር ሙሉ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና በውሃ አጠቃቀም እንዲሁም በሌሎች ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩት ሥራ ውጤት ተኮር መሆን አለበት ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ከተቋማት ጋር በመተሳሰር ለቴክኖሎጂ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለቱሪዝም፣ ለሕክምናና ለማዕድን ዘርፎች ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ለማጠናከርና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መትጋት እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲዎች ስራዎችና ዕቅዶች ውጤታማና ችግር ፈቺ መሆን አለባቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤
ዕቅዶች ተግባር ተኮር እንዲሆኑና ሥራዎችንም መመዘን እንዲቻል ሁሉም ሠራተኞች ሊወያዩበትና የጋራ ሊያደርጉት ይገባል ነው ያሉት።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሀብት ብክነት እንዳይኖር በጥንቃቄ ማቀድና መጠቀም እንደሚገባ አክለዋል።
ፈጻሚን ማበረታታት፣ ሥልጠና መስጠት፣ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን ማስፋትና ከማኅበረሰቡ ጋር በቅርበት መወያየት ዩኒቨርሲቲዎች ሊፈጽሟቸው የሚገቡ ተግባራት እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ የሶስት ቀናት ውይይታቸውን ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ያጠናቀቁ ሲሆን
በተልዕኮና ልየታ የተሰጧቸውን ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ከፍ ባለ አገራዊ ኃላፊነት ለማሳካት ተግተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
የአገርን ሠላምና አንድነት ለማስከበር በየጦር ግንባሩ ለሚዋደቀው የአገር መከላከያ ሠራዊት በደጀንም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ትምህርትና እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውን የወደፊት አገር ተረካቢ ታዳጊ ሕጻናት ዓለም አቀፍ ሕግን በመጻረር ለውትድርና እየመለመለ ለጦርነት የሚማግደው ኃይል በሕግ እንዲጠየቅም በአፅንኦት ጠይቀዋል።
መንግሥት ቀጣናዊ አቅም እየፈጠረ የሚሰራውን ሥራ በመደገፍ ኢትዮጵያን በመከፋፈል ለማዳከም የሚሰሩትንና የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎችን ጫና አጥብቀው እንደሚቃወሙም በአቋም መግለጫቸው ገልጸዋል።
"በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ተፈጥሯዊ መብታችንን በመጠቀም ወደ ብልጽግና ጉዞ ለጀመርነው ጉዞ መሰረት እንዲሆነንና የአገራዊ መገለጫም በመሆኑ ፍትሃዊ ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥ የምሁራን ሚናችንን እንወጣለን"፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራምን ለማስቀጠልና በሳይንሳዊ ምርምር በመደገፍ በላቀ ደረጃ ለማስቀጠልም የድርሻችንን እንፈጽማለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲዎቹ በ2013 ዓ.ም ያጋጠሙትን ዓለም አቀፉ ወረርሽኝና አገራዊ የሠላም ተግዳሮቶች ያደረሱትን ፈተና በመሻገር በመማር ማስተማሩ ሂደት የተፈጠረውን መስተጓጎል ለማካካስ የተጀመረውን ፕሮግራም በ2014 የትምህርት ዘመንም በሙሉ አቅምና ፍላጎት ለመስራት ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡