አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ ለሰራዊቱ ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ ለሰራዊቱ ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶች ድጋፍ አደረገ
ደሴ፤ ሐምሌ 30/2013(ኢዜአ) አርቲስት ታምሩ ብርሃኑ ለመከላከያ ሰራዊትና ፀጥታ አባላት የሚውል ከ200 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ቁሶች ድጋፍ አደረገ።
አርቲስቱ ድጋፉን ያደረገው በደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በኩል ነው።
በድጋፍ ርክክቡ ስነ-ስርዓት አርቲስቱ እንደገለጸው፤ አሸባሪው ትህነግ በከፈተው ጦርነት ሀገር እንዳትፈረስ ህይወቱን አሳልፎ በመስጠት መስዋዕት እየከፈለ ያለውን መከላከያ ስራዊት ሁሉም መደገፍና ደጀን መሆን ይኖርበታል፡፡
ከዚህ በፊት በሆስፒታሉ ህክምና እያገኙ የነበሩ መከላከያ ሰራዊቱን ሲጎበኙ ያስተዋለው የቁሳቁስ ክፍተት ለመሙላት እንዲያግዝ ያሰባሰበውን ድጋፍ ዛሬ አስረክቧል፡፡
ከድጋፉ መካከል 120 ፍራሽ፤ 180 ብርድ ልብስና ሌሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሶች እንደሚገኙበት ያመለከተው አርቲስት ታምሩ፤ ከራሱና ጓደኞቹ ያሰባሰባቸው እነዚህ ቁሶች ከ200 ሺህ ብር በላይ እንደሚገመቱ አስታውቋል፡፡
መከላከያ ሰራዊቱን በሙያ ከምደግፈው በተጨማሪ ህብረተሰቡን በማስተባበር በገንዘብም ለመደገፍ ዝግጁ ነኝ ብለዋል፡፡
የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ልዑል መስፍን ፤ ድጋፉ የሆስፒታሉን ችግር ያቃልላል ብለዋል፡፡
ሆስፒታሉ ለመከላከያ ሰራዊትና ፀጥታ አባላት የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ለሀገሩና ህዝብ ሲል መስዋዕት እየከፈለ ያለውን መከላከያ ሰራዊት መደገፍ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡
ሆስፒታሉ የመድሃኒትና የሌሎች የግብዓቶች እጥረት እንዳለበት የተናገሩት ዶክተር ልዑል፤ ችግሩን ለማቃለል መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር የሚያርገው ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመከላከያ ሚኒስቴር የምድር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ የጤና ማዕከል ኃላፊ ብርጋዴል ጀነራል ይልማ መኳንንቴ፤ አርቲስቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ሆስፒታሉ ለሰራዊቱ የሚሰጠው ያልተገደበ የህክምና አገልግሎት የሚደነቅ ነው ያሉት ኃላፊ፤
ሁሉም የሚችለውን በማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።