የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ በግንባር ለሚገኘው ሠራዊት ተጨማሪ አቅምና ጉልበት እየሆነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ በግንባር ለሚገኘው ሠራዊት ተጨማሪ አቅምና ጉልበት እየሆነ ነው
ደባርቅ ሐምሌ 30/2013(ኢዜአ) "የኢትዮጰያ ህዝብ በግንባር ለሚገኘው የጸጥታ ሃይል እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጨማሪ አቅምና ጉልበት እየሆነ ነው" ሲሉ የአዲ አርቃይ ማይፀብሪ ግንባር ሎጂስቲክስ አስተባባሪ አስታወቁ።
የሰሜን ጎንደር ዞን ነዋሪዎች ለሰራዊቱ ድጋፍ እንዲውል ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ አዋጥተዋል።
አስተባባሪው አቶ አንዳርጌ ዘነበ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ህዝባዊ ድጋፉ ሠራዊቱ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ወኔ እንዲላበስ እያገዘ ነው።
በግንባሩ የመከላከያ ሠራዊት፣ የልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ጥምረት ፈጥረው የአሸባሪው ትህነግ ርዝራዥ እየተፋለሙ ይገኛሉ።
"በግንባር ለሚገኘው ሃይል ማህበረሰቡ ገንዘብ በማዋጣት፣ ምግብና መሰል ሎጂስቲክስ በማቅረብ ተጨማሪ ጉልበት እየሆነው ይገኛል" ብለዋል።
በአሸባሪው የተከፈተው ጦርነት ህዝቡን አንድ አድርጎ የሃገር ሉአላዊነትን ለማስከበር የአብሮነት ስሜትና ንቅናቄ ፈጥሯል።
አስተባባሪው እንዳመለከቱት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አስፈላጊውን ግብዓት ከማቅረብ በዘለለ በአካል ተገኝቶ እያበረታታ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
"በአዲ አርቃይ ማይፀብሪ ግንባር የተሰለፈው ሃይል የሽበር ቡድኑን በአጭር ጊዜ መደምሰስ እንዲችል አስፈላጊው ግብዓት ሁሉ እየቀረበ ይገኛል" ብለዋል።
እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከ3ሺህ በላይ ካርቶን ብስኩት፣ 190 ኩንታል ስኳር፣ 300 ኩንታል በሶ፣ 327 ሰንጋ፣ 825 በግና ፍየል ቀርቦ በግንባር ለሚገኘው ሠራዊት እየተሰራጨ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪ 3 ሺህ 660 ብርድ ልብስ፣ 3 ሺህ 660 ሽርጥ፣ 3 ሺህ 660 ጫማ፣ 1ሺህ የዝናብ ልብስና መሰል ቁሶች በግንባር ለሚገኘው ሃይል ተልኳል ብለዋል።
"እየቀረበ ያለው ሎጅስቲክስ ሳይቆራረጥ በሰዓቱና በፍትሃዊነት እንዲደርስ በየደረጃው የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ጥብቅ ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ" ብለዋል
በጠላት ሃይል ላይ እየተወሰደ ያለው ጠንካራ እርምጃ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን የደጀንነት ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ አንዳርጌ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል የሰሜን ጎንደር ዞን አቅርቦት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ወገኔ አማረ እንዳሉት፤ ከዞኑ ህዝብ በግንባር ለሚገኘው ሃይል 155 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ እስካሁን ከገጠሩና ከተማው ነዋሪዎች ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተዋጥቷል።
በቀጣይ በዕቅዱ የተያዘውን ሃብት ሙሉ በሙሉ ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ በአሸባሪው የትህነግ ርዝራዥ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
"አሁን ባለው የህልውና ዘመቻ ሴቶችን፣ ወጣቶችንና ሌላውም የህብረተሰብ ክፍልን በማስተባበር የስንቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው" ያሉት ደግሞ የዞኑ ሃብት አሰባሳቢ ወይዘሮ ባንችአምላክ አምላኩ ናቸው።
በስንቅ ዝግጅቱም ዳቦ ቆሎ፣ ቆሎ፣ ደረቅ እንጀራ እየተዘጋጀ ከመሆኑም ሌላ ህብረተሰቡ በደም ልገሳ ጭምር እየተሳተፈ ይገኛል።
በግንባር ያለውን ሃይል በአጭር ጊዜ በጠላት ላይ ውጤታማ ድል እንዲቀዳጅ በደጀኑ ህዝብ መተማመን እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለዚህም የሎጂስቲክስ አቅርቦቱ ባልተቆራረጠ መንገድ እንዲደርስ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ "ይህም እስከ መጨረሻው የድል ቀን ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉ አስታውቀዋል።