በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል
አበባ አበባ ሃምሌ 30/2013(ኢዜአ) በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት የኤሌክትሪክ ሃይል ኤክስፖርት በማድረግ ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።
ተቋሙ በአገር ውስጥ ባቀረበው ጅምላ ሽያጭ ከ13 ቢሊዮን 267 ሚሊዮን 104 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡንም አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው በጀት ዓመት ተቋሙ ከተለያዩ ማመንጫዎች ያመረተውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ በጅምላ በማቅረብ ረገድ ከዕቅዱ በላይ አከናውኗል።
በዚህም ለጎረቤት አገራት በበጀት ዓመቱ ካቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል 80 ሚሊዮን 787 ሺህ 600 ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 90 ሚሊዮን 532 ሺህ 669 ዶላር ተገኝቷል።
ይህ ገቢ የተገኘው ለሱዳንና ለጅቡቲ ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሞገስ ከአሁን በፊት በነበሩ የውጭ ገበያ ሽያጮች ከ70 ሚሊዮን ዶላር በላይ የተሸጠበት ጊዜ አለመኖሩን አስታውሰዋል።
ተቋሙ ለውጭ ከሚያቀርበው ኃይል በተጨማሪ በአገር ውስጥ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ፋብሪካዎች፣ ለባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ለኢትዮ-ቴሌኮምና መሰል ተቋማት ኃይል በጅምላ ይሸጣል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ በጅምላ ከሚቀርበው የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት 13 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን 774 ሺህ 591 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 13 ቢሊዮን 267 ሚሊዮን 104 ሺህ 524 ብር ተገኝቷል።
ተቋሙ በአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ በጅምላ በማቅረብ የነበረው አፈፃፀም 101 ነጥብ 1 መሆኑንና ይህም ከእቅዱ በላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ አገር ያለው የኃይል ማመንጫ ግንባታ፣ ኃይል የማምረትና የተመረተውንም ሳይባክን ወደ ግሪድ አስገብቶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራው እያደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከኤሌክትሪክ ኃይል የሚገኘው ገቢ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ በመምጣቱ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተቋሙ የሚሰራቸውን ፕሮጀክቶች በራሱ በጀት መከወን እንደሚችል ያመላክታል ብለዋል።