ቀጥታ፡

ሊዲያ ታፈሰ በዓለም ዋንጫው የመጀመሪያ ጨዋታዋን በዋና ዳኝነት መራች

አዲስ አበባ ነሃሴ 3/2010 ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ፈረንሳይ እየተካሄደ በሚገኘው ዘጠነኛው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ የመጀመሪያ ጨዋታዋን በመሐል ዳኝነት መርታለች። 16 ብሔራዊ ቡድኖች እየተሳተፉበት የሚገኘው የዓለም ዋንጫ ከሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ሊዲያ ትናንት ማምሻውን በምድብ አንድ የኒውዝላንድና አዘጋጇ ፈረንሳይን ጨዋታ የመራች ሲሆን ጨዋታው ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል። ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ በዓለም ዋንጫው የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የዳኞች ኮሚቴ ግንቦት 2010 ዓ.ም ውድድሩን እንዲመሩ ከ21 አገራት ከተመረጡ 15 ሴት ዋና ዳኞችና 30 ረዳት ዳኞች መካከል አንዷ ናት። ፊፋ በውድድሩ እንዲያጫውቱ ከመረጣቸው የአፍሪካ አገራት ሁለት ዳኞች መካከል አንዷ ስትሆን ዛምቢያዊቷ ሌንግዌ ግላዲየስ ሌላኛዋ ውድድሩ ላይ እንድታጫውት የተመረጠች አፍሪካዊ ዳኛ ናት። ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት አህጉራዊ እና አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የማጫወት ልምድ አላት። ከሶስት ዓመት በፊት በካናዳ በተካሄደው የዓለም ሴቶች ዋንጫ እና የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ውድድሮች ላይ ጨዋታዎችን መምራት ችላለች። ሊዲያ ከሁለት ዓመት በፊት በዮርዳኖስ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዓለም ዋንጫ ላይም ተመርጣ በውድድሩ የተካሄዱ ጨዋታዎችን መርታለች። ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ የ2008 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ዳኛ ተብላ መመረጧም ይታወቃል። ፊፋ በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በሩሲያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያዊውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ እንዲያጫውት መምረጡ የሚታወስ ነው። የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም