የትህነግን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ ተነሳስተናል - ኢዜአ አማርኛ
የትህነግን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ ተነሳስተናል
ደሴ፤ሐምሌ 30/2013(ኢዜአ) ልምድና አቅማችንን በመጠቀም የትህነግን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ ተነሳስተናል ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚኖሩ የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት አስታወቁ።
ከአባላቱ መካከል አቶ ዓባይ ደርሶ በህወሓት ሴራ ያለ ጡረታና ጥቅማጥቅም ከሠራዊቱ መሰናበታቸውን ያስታወሳሉ።
ኢትዮጵያን ከጠላት ለመታደግ የሠራዊቱ አባል በመሆን መስዋዕትነት ከፍለዋል።
በቀድሞው ጦር ያገኙትን እውቀትና ልምድ ተጠቅመው የአሸባሪውን የትህነግ ሴራ ለማክሸፍ በሚካሄደው ትግል ለመሳተፍ ተነሳስቼያለሁ ነው ያሉት አቶ ዓባይ።
አሸባሪው ቡድንን ለመደምሰስ በሚደረግ ትግል እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል የሀገርን ደህንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ለኢዜአ ሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
"ትህነግ ገና ሲመሰረት የተከተለው ህዝብን በዘርና ቋንቋ የመከፋፈል ስትራቴጂው አገር ከማፍረስ ጋር የተያያዘ ነው" ያሉት አቶ አባይ፣ ሀገር ወዳድና ኢትዮጵያዊ ስሜት ያላቸውን የሠራዊቱን አባላት፣ ምሁራንን፣ ፖለቲከኞችና ባለሃብቶችን ሲገድል እንደነበረም አስታውሰዋል።
"ዕድሜ ልኩን በኢትዮጵያ ላይ ሲፈጽም የቆየው ግፍና በደል አልበቃው ብሎ ዛሬም ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር የወጠነውን ሀገር የማፍረስ ሴራ ሁላችንም ተባብረን የምናከሽፍበት ወቅት ላይ ነን" ብለዋል። አረጋግጠዋል።
ሃምሳ አለቃ ይርጋ ማርዬ በበኩላቸው "ለሀገራችን ዋጋ ከፍለን ዳር ድንበሯን ባስከበርን አሸባሪው ትህነግ እንደ ጠላት ቆጥሮን ለስቃይና ለችግር ዳርጎናል" ብለዋል፡፡
ያለ ጡረታና ጥቅማጥቅም በባዶው በመበተናቸው የተወሰነው የሠራዊት አባል ለጎዳናና ለልመና በመዳረጉ እስካሁን ድረስ በችግር ውስጥ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
"በእኛ ላይ ያደረሰው ግፍና ስቃይ፣ የኢትዮጵያን ሀብት የመዘበረውና፣ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የፈጸመው አስነዋሪ ጥቃት ሳይበቃ አሁን ሀገር ለማፍረስ የሚያርገው መፍጨርጨር አይሳካለትም" ብለዋል፡፡
"የጦሩ አባል በነበርኩበት ወቅት የነበረኝን ልምድ እውቀት ተጠቅሜ የአሸባሪውን ርዝራዥ ለመቅበር ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ ጋር ለመሰለፍ ተነሳስቼያለሁ " ነው ያሉት።
ትህነግ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያልፈጸመው ግፍና ጭቆና ባለመኖሩ ሁላችን አንድነታችንን ጠብቀን ቡድኑን መደምሰስ አለብን ያሉት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ መቶ አለቃ ካሣ ደስዬ ናቸው፡፡
"አሸባሪውን ቡድን ከመንግስትና መከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ተቀናጅተን የገባበት ገብተን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት ዝግጁ ነን" ብለዋል።
ቡድኑ አለሁልህ ለሚለው የትግራይ ህዝብ እንኳ እንደማይጠቅም ህጻናትን ለጦርነት በመማገድና ሰብዓዊ ድጋፍ በመከልከል በተግባር ማሳየቱን ጠቅሰው፤ የትግራይ ህዝብም ከእህት ወንድሞቹ ኢትዮጵያዊያን ጎን በመሆን ቡድኑን በቃህ ሊለው ይገባል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላቱ በተደራጀ አግባብ ወደ ግንባር ለመዝመት ከመንግስት ጋር እየሰሩና ነባር የመከላከያ ሠራዊት አባላትን እያሰባሰቡ መሆናቸውንም አስታወቀዋል፡፡