አማራ ክልል ሰርጎ የገባው የአሸባሪው ህወሀት ታጣቂ ከአማራ ሚሊሻና ልዩ ሀይል አቅም በታች ነው - ኢዜአ አማርኛ
አማራ ክልል ሰርጎ የገባው የአሸባሪው ህወሀት ታጣቂ ከአማራ ሚሊሻና ልዩ ሀይል አቅም በታች ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ) አማራ ክልል ሰርጎ የገባው የአሸባሪው ህወሀት ታጣቂ ከአማራ ሚሊሻና ልዩ ሀይል አቅም በታች መሆኑን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። አሸባሪው ህወሀት እስካልጠፋ ድረስ "ወደፊትም የሀሰት ወሬና ማወናበድ አይጠፋም ህዝቡ ከዚህ ውዥምብር መውጣት አለበትም" ተብሏል።
የኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሰራዊት ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
አሸባሪው ህወሓት በራያ በኩል በጉባ ላፍቶና ሀብር ወረዳዎች በአካባቢው ህዝብ የደረሰበትን ምት መቋቋም ሲሳነው ትጥቁን እየጣለ መፈርጠጡን ገልጸዋል።
የአማራ ሚሊሻ የማረካቸውን የህወሃት ሰርጎ ገቦች ለመከላከያ ሠራዊት ያስረከበ መሆኑን ጠቁመው፤ የማረኩትን የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ራሳቸውን እንዲያጠናክሩበት መደረጉን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የደረሰበትን ኪሳራ መቋቋም አቅቶት የፈረጠጠው የአሸባሪው ሀይል ወደ ጋሸና፣ ተኩለሽና ቁልመስክ በመሸሽ በለመደው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ህዝቡን እያወናበደ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን እስካልጠፋ ድረስ የሀሰት ወሬና ማወናበድ ስለማይጠፋ ህብረተሰቡ ህጋዊ ከሆነ የመንግሰት አካል የሚሰጠውን መረጃ ብቻ በመከተል ከውዥንብሩ መውጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ አሸባሪው የህወሃት ቡድን በተከዜ በኩል በከፈተው ጥቃት ከፍተኛ ኪሳራ ስለደረሰበት ካሁን በፊት እንዳደረገው አስከሬን በሲኖ ትራክ ጭኖ መሄድ አልቻለም።
ከዚህም ባለፈ ምንም ዓይነት የውጊያ ስልት የማያውቁ ንጹሃንን በግድ ወደ ትግል በማስገባት ተከዜ ላይ የውሃ ሲሳይ ሆነው እንዲቀሩ ማድረጉን ጠቁመው፤ በውጊያ የሞቱትን መቅበር ስላልቻለ አስክሬናቸውን ተከዜ ወንዝ ላይ እንደጨመረ ተናግረዋል።
ይህ እኩይ ድርጊቱ አልበቃው ብሎ በለመደው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በተሳሳተ መረጃ "አለም አቀፉን ማህበረሰብ ጭምር ማወናበድ ጀምሯል" ብለዋል።
በተከዜ ወንዝ አካባቢ ምንም አይነት የመንግስት ሀይል እንደሌለ ሁሉም ሊያውቅ ይገባልም ብለዋል ኮሎኔል ጌትነት።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለሠብዓዊ እርዳታ የሚላከውን ገንዘብ ለትጥቅ ትግል ይጠቀምበት እንደነበረው ሁሉም ዛሬም በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚፈፅመውን ግፍ ነገ ታሪክ ይወቅሰዋል ብለዋል።