ለጤና ተቋማት ቀልጣፋ መድሃኒትና የሕክምና ግብዓት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ለጤና ተቋማት ቀልጣፋ መድሃኒትና የሕክምና ግብዓት ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ፕሮግራም ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) ለጤና ተቋማት መድሃኒትና የሕክምና ግብዓቶቸን በተቀላጠፈ መልኩ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል "አቀርባለሁ" /I-SUPPLY/ የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ ሆነ።
ፕሮግራሙን የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በፕሮግራም ማስጀመሪያ ስነ ሥርዓቱ ላይ በአገሪቷ የጤና አገልግሎት ሥርዓትን የሚያሻሽሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ለጤና ተቋማት የመድሃኒትና የሕክምና መገልገያ ግብዓቶችን በማሟላት ለተገልጋዩ ማኅበረሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ከተግባራቱ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
"አቀርባለሁ" /I-SUPPLY/ የተሰኘው ፕሮግራም ከተለያዩ ተቋማትና ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት ብሎም በቴክኖሎጂ በመታገዝ አቅርቦቱን የማጠናከር ስራ መስራት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
የመድሃኒትና የሕክምና መሳሪያዎች አቅርቦት የሚሻሻልበትን ስርዓት በመዘርጋት ማኅበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል የሚያደርግ እነደሆነም አክለዋል።
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ የጤና ተቋማት ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ለማኅበረሰቡ መስጠት እንዲችሉ መድሃኒትና የሕክምና መገልገያ ግብዓቶችን ማሟላት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር እንደ አገር ካለው ሰፊ የሕክምና አገልግሎት ፍላጎት አንጻር ትልቅ የመድሃኒት መጋዘን እንዲኖር ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል።
የአቅርቦት ሰንሰለቱን የማሻሻልና የማጠናከር ስራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
I-SUPPLY ወይንም "አቀርባለሁ" የተሰኘው ፕሮግራም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የጤና ተቋማት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።