ቀጥታ፡

በመተከል ዞን አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው የመከላከያ ሠራዊቱን ለሚቀላቀሉ ወጣቶች ሽኝት ተደረገላቸው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን አገራዊ ጥሪውን ተቀብለው የመከላከያ ሠራዊቱን ለሚቀላቀሉ ከ1 ሺህ 300 በላይ ወጣቶች ዛሬ ሽኝት ተደርጎላቸዋል።

የመተከል ዞን አስተዳዳሪ ጋሹ ዱጋዝ አገራዊ ጥሪውን የተቀበሉ ወጣቶችን አመስግነው "አገር ለማፍረስ የቋመጡ ባንዳዎች"ን ተልዕኮ ለማክሸፍ የሚገጥሟችሁን ፈተናዎች በጽናት በማለፍ በድል እንደምትመለሱ እምነቴ ነው ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ቀልቤሳ ዋቅጅራም ወጣቶቹ ኢትዮጵያን ለማሻገር ትልቅ አደራ እንደተጣለባቸው በመግለጽ ተልዕኳቸውን በጀግንነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው ወጣቶቹ በድል እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት በመግለጽ 'ይህንን አደራ መቀበላችሁ በራሱ ትልቅ ድል ነው'  በማለት ሸኝተዋቸዋል።

ለወጣቶቹ ከስንቅ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል የገቡ ሲሆን፤ ዘመቻው ኢትዮጵያን የማዳን ጥሪ መሆኑንና ኢትዮጵያን አሸናፊ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ወጣቶቹም የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች "ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ ለቀረበው አገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት የአገር መከላከያ ሠራዊትን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም