ሽብርተኛው ህወሓትን ለመጨረሻ ጊዜ በመቅበር የአባቶች ታሪክ ይደገማል - ኢዜአ አማርኛ
ሽብርተኛው ህወሓትን ለመጨረሻ ጊዜ በመቅበር የአባቶች ታሪክ ይደገማል
ደሴ፣ ሐምሌ 29/2013( ኢዜአ ) የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን ድጋፍና አንድነቱን በማጠናከር ሽብርተኛው ህወሓትን ለመጨረሻ ጊዜ በመቅበር የአባቶቹን ታሪክ እንደሚደገም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች አባላት ተናገሩ።
አርበኞቹ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ባህልና እሴቱን ጠብቆ ለማስቀጠል አብሮነቱንና የሀገሩን ህልውና እንዲያስጠብቅም አርበኞች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጽህፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ተተኪ አርበኛ አየለ ወልደጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት አባቶች በአጥንትና በደማቸው ያቆዩዋትን አገር ለማፍረስ እየሰራ ነው።
ቡድኑ የስልጣን ጥሙን ለማርካት ሩጠው ያልጠገቡ፣ ነፍስ ያላወቁና ደብተር መያዝ ያለባቸውን ህጻናት ሳይቀር ለጦርነት እየማገደ በመሆኑ አዝነዋል።
"ወገናችን የትግራይ ህዝብ ለጥቂት ግለሰቦች ብሎ ልጆቹን በየበረሃው ማስጨረስ የለበትም" ያሉት ዋና ጸሐፊው ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን እንዲታገለው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
"ወጣቱ ከመንግስት ጋር በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ እስከ ግንባር ዘምቶ ሀገሩን መታደግና የአባቶቹን ታሪክ መድገም ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡
ሌላው ተተኪ አርበኛ ሃምሳ አለቃ አለማየሁ አበበ በበኩላቸው ዕድሜያቸው ቢገፋም ሽብርተኛው ህወሓትን ለመደምሰስ በሚደረገው ትግል ለሠራዊቱ ስንቅና ትጥቅ በማቀበል ደጀን ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
"አገር በባንዳ ስትወረር ዝም ብዬ አላይም" ያሉት ተተኪ አርበኛው፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን ድጋፍና ያሳየውን አንድነት እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
"በዚህም ቡድኑን ለመጨረሻ ጊዜ በመቅበር የአባቶቹን ታሪክ መድገም አለበት" ሲሉ አሳስበዋል።
ሽብርተኛው ህወሓት እኔ ያልመራኋት ሀገር ትውደም በሚል የያዘው ግትር ሀሳብ ነውረኛና የኢትዮጵያን ባህልና እሴት የሸረሸረ መሆኑንም አርበኛው ገልጸዋል፡፡
"አገራችንን ከባንዳና ወራሪ መጠበቅ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን አገርን ከመፈራረስ መታደግና የህልውና ጉዳይ ነው" ያሉት ደግሞ ተተኪ አርበኛ ወይዘሮ ሰርካለም ጥበቡ ናቸው፡፡
በመሆኑም ሴት ወንድ፤ ትንሽ ትልቅ ሳይባል ሁሉም የበኩሉን እገዛ በማድረግ ኢትዮጵያን ከአጥፊዎች መታደግ እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡
"ህጻናት በጦርነት ሲማገዱ ማየት ልብ ይሰብራል" ያሉት ወይዘሮ ሰርካለም፣ የትግራይ እናቶች አሸባሪውን ቡድን ከጥፋት መንገዱ እንዲያስቆሙ መክረዋል።
ምዕራባዊያን በተሳሳተ መረጃ ተነስተው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ከማድረግ ይልቅ አሸባሪው ቡድን የሚፈጽመውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥቃት እንዲያስቆሙ ጠይቀዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጽህፈት ቤት ከ1ሺህ 500 በላይ አባላት እንዳሉት ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡