ቀጥታ፡

ጋዜጠኞች ከሙያዊ ኃላፊነታቸው ባሻገር በአገር የማዳን ዘመቻው የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል

ሐምሌ 29/2013 (ኢዜአ) ጋዜጠኞች ከሙያዊ ኃላፊነታቸው ባሻገር እንደ ዜጋ በአገር የማዳን ዘመቻው ላይ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ  ሰይፈ ደርቤ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት (ኢዜአ) ሰራተኞች የ2013 ዓ.ም የስራ አፈፃፀም እና የ2014 እቅድ መነሻ ሃሳብ ላይ ውይይት አካሄደዋል።

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የህወሃት አሸባሪ ቡድን በመመከት አገር የማዳን ዘመቻውን ስኬታማ ለማድረግ ጋዜጠኞች ከሙያቸው በተጨማሪ እንደ ዜጋ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት "እኔ ወታደር ነኝ" በሚል መርህ የተጀመረው ብሔራዊ ንቅናቄ ቀጣይነት እንዲኖረው በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ለዚህም የኢዜአ ሰራተኞች ሙያዊ ኃላፊነታቸውንና ሀገራዊ ግዴታቸውን በስኬት ለመፈፀም ተጨማሪ ጊዜ ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኢዜአ ከመፍረስ አደጋ ወጥቶ በለውጡ ሂደት በርካታ ሀገራዊ ኃላፊነቶችን በስኬት በመወጣት ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ሰይፈ፤ ለዚህም የተቋሙ ሰራተኞች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢዜአ በትግራይ ከህግ ማስከበር ዘመቻ እስከ አገር የማዳን ተልእኮ እንዲሁም በህዳሴ ግድብ፣ ኮሮናን በመከላከል ሂደትና አጠቃላይ በአገር ሰላምና መረጋጋት ተግባራት ውጤታማ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ሰራተኞች በተለይ የእርስ በርስ ትብብራቸውን በማጠናከር ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

ኢዜአ አዲስ ላስገነባው ግዙፍ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የስቱድዮ ግብአት ለማሟላት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘመናዊ ካሜራዎችና ድሮኖች ግዥ ማከናወኑን ተናግረዋል።

ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት የገቢ አማራጮችን የማስፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም እንዲሁ።

በተያዘው በጀት ዓመት ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም ዋና ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

የኢዜአ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የተቋሙን ስራዎች በማስተዋወቅና ይበልጥ ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን የሚከበር ይሆናል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢዜአ የቦርድ አመራር ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ፣ ኢዜአ ከመፍረስ አደጋ ወጥቶ ባለፉት ሶስት አመታት ያስመዘገበው ስኬት እና አሁን ያለበት ደረጃ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እና በሰላም ሚኒስቴር ተቋሙ የተሰጠውን እውቅና አንስተው፤ እውቅናው ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውና በቀጣይም ለበለጠ ስራ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም "ኢዜአ በቀጣይ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን እንሻለን ለዚህም ቦርዱ የተቻለውን ሁሉ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም