ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የጥጥ ምርትን ለማዘመን ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር ያስፈልጋል

አዲስ አበባ ፣ሃምሌ 29/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የጥጥ ምርትን ለማዘመን ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጥጥ ምርት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱም በኢትዮጵያ የጥጥ ምርትን ለማዘመን ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ተካ ገብረየስ፤ በውይይቱ ላይ እንዳነሱት ጥጥ በኢትዮጵያ ከባህላዊ አልባሳት ጋር በተያያዘ የቆየ ታሪክ እንዳለው አንስተው ሆኖም የአገሪቷ የገቢ ምንጭ በማድረግ ብዙ እንዳልተሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ጥጥ ከማምረት አቅሟ እስካሁን ማልማት የቻለችው ሶስት በመቶ ብቻ ነው።

በመሆኑም በዘርፉ እየታየ ያለውን ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መመካከር አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርጎ ኬሚካሎችን ለአምራቾች ማድረሱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ፤ የጥጥ ምርት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የተለያዩ ችግሮች እየገጠሙት መሆኑን አንስተዋል።

በዘርፉ የተሰማሩት አልሚዎች ያሉባቸውን የግብአት እጥረትና የመሰረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የጥጥ አመራረትን ለማዘመንም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራር መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።

ለዘርፉ ስኬታማነት የመንግስት ጥረት እንዳለ ሆኖ የባለሃብቶችም ድጋፍና እገዛ ወሳኝ መሆኑ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም