ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ሃይሎች ጥረት ህዝባዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ሃይሎች ጥረት ህዝባዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር አድርጓል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ሃይሎች ጥረት ህዝባዊ አንድነት እንዲጠናከር አድርገዋል" ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሣምንታዊ መግለጫ ላይ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ክንውኖችን አንስተዋል።
በሳምንቱ የተመድ የሰብዓዊና የአስቸኳይ ዕርዳታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት /ኦቻ/ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም በሰሜን ኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታዎች የተኩስ ማቆም እርምጃውን አሸባሪው ህወሓት ባለመቀበሉ የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ መስተጓጎሉን አቶ ደመቀ አስታውሰዋቸዋል።
በአማራና በአፋር ክልሎች በተከፈተ ጥቃት ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ቢፈናቀሉም፤ ኦቻን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አለማውገዛቸውና ከአሰራር ስርዓት ውጭ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እንዳሉም ገልጸውላቸዋል።
ማርቲን ግሪፊትስ በበኩላቸው ሠብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩና የመንግስትን የተኩስ አቁም እርምጃ ማድነቃቸውን አምባሳደር ዲና አንስተዋል።
በሠብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በኩል የተስተዋሉ ችግሮች እንደሚቃለሉ መግለጻቸውንም እንዲሁ።
በሌላ በኩል የአሜሪካው ረድኤት ድርጅት /ዩ.ኤስ.ኤድ/ ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ጉብኝት "በእኛ በኩል ስኬታማ ዲፕሎማሲ ነበር" ብለዋል።
ሃላፊዋ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት በስራ መደራረብ ሳቢያ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደማያገኙ ተነግሯቸው እንደነበረም አንስተዋል።
ሳማንታ ፓወር በጉብኝታቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የኮቪድ ክትባት መለገሳቸውን፣ በአዳማ የሚገኘውን የእርዳታ ምግብ ክምችት መጎብኝታቸውን ገልጸው፤ ጉዳያቸው ሠብዓዊ እንጂ ፖለቲካዊ እንዳልነበር አስረድተዋል።
በዚህም ከጉዳያቸው ጋር የሚገናኙ የስራ ሃላፊዎችን ለአብነትም የሠላም ሚኒስትሯን ሙፈሪያት ካሚልን ማግኘታቸውን፤ በውይይታቸውም አሸባሪው የህወሓት ቡድን ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪዎችን ውድቅ ማድረጉን በመጨረሻም በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ከጅምሩ አንስቶ በዝርዝር አስረድተዋቸዋል ነው ያሉት።
ለአሁናዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ መነሻው የአሸባሪው ህወሓት ፀረ ሠላምና ፀረ ለውጥ አመለካከት መሆኑ እንደተገለጸላቸውም አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል።
ሃላፊዋ 'አመጣጤ እንደሚወራው የፖለቲካ ወይም መንግስት መቀየር ሳይሆን ሠብዓዊነት ብቻ ነው' ማለታቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና፤ በሱዳን በኩል መንገድ የማስከፈት ጉዳይን እንዳላነሱ አክለዋል።
ይልቁንም ረጅም ጊዜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት መሻከር እንደሌለበት ማንሳታቸውን፤ ህወሓት በአጎራባች ክልሎች የሚያደርገውን ወረራም መኮነናቸውን ገልጸዋል።
በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሠላም ጓድ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ መሆኑን፤ ዓላማውም በሠብዓዊ ድጋፍና ገፅታ ግንባታ በመሳተፍ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መሆናቸውን ለማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል።
በምጣኔ ሀብት ረገድ የኢትዮ-ናይጄሪያ የጋራ የንግድ ምክር ቤት ለመመስረት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ከናይጄሪያ አቻው ጋር መፈራረሙን፤ ይህም ለሁለትዮሽ ትስስር መጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዘርፍ የዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ በዲፕሎማሲና በገንዘብም እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ለአብነትም በደቡብ ሱዳን ጁባ 80 ሺህ ዶላር፤ በአሜሪካም በቀን 124 ሺህ ዶላር መሰብሰቡን አስታውሰዋል።
አምባሳደር ዲና በሣምንቱ ከ500 በላይ ዜጎች ከምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ የተለያዩ አገራት ከስደት ተመልሰዋልም ብለዋል።
ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ሃይሎች እርዳታ የማስከልከል፣ የአሜሪካ ነጻ ገበያን እንዳትጠቀም የማሳገድን ጨምሮ ሌሎች ጥረቶች ማድረጋቸውን የገለጹት ቃል አቀባዩ ይሁንና ሃሳብ እንጂ ገቢራዊ አጀንዳ እንደሌለ ተናግረዋል።
ይልቁንም ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ሃይሎች የሕዝብ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር አድርገዋል ብለዋል።
ለአብነትም በሁለተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትና በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ አገሪቷ ትበታተናለች በማለት ሲያሟርቱ የነበሩ ሃይሎች ቢኖሩም ሕዝቡ ግን አንድነቱን ይበልጥ አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።