ጀግኖች አባቶቻችን ያስረከቡንን ሀገራችን አናስደፍርም! - ኢዜአ አማርኛ
ጀግኖች አባቶቻችን ያስረከቡንን ሀገራችን አናስደፍርም!
ጎባ ሐምሌ 28/2013 (ኢዜአ) ጀግኖች አባቶቻችን ያስረከቡን ሉዓላዊት ሀገራችን በማንም አናስደፍርም! ሲሉ የባሌ ሮቤ አካባቢ ወጣቶች አስታወቁ።
በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ አስተዳደር ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሠለፍ አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ለመፋለም የተዘጋጁ የሁለተኛው ዙር ዘማች ወጣቶች ተሸኝተዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በፍላጎታቸው ለመቀላቀል ከተዘጋጁ ወጣቶቹ መካከል አህመድ ጀማል፤ ጀግኖች አባቶቻችን ያስረከቡንን ሉዓላዊት ሀገራችንን በአሸባሪ ቡድንና የውጭ ጠላት አትደፈርም ብሏል።
ለዚህም ከሀገር መከላከያ ጎን በመሠለፍም መስዋዕትነት ለመክፈል በራሱ ተነሳሽነት መወሰኑን ነው የተናገረው፡፡
መንግስት የሀገሪቱን ሉኣላዊነት ለማስከበር ተገዶ የገባበት ህግን የማስከበር እርምጃ ትክክለኛ መሆኑን ስለምረዳ የሚጠበቅብኝን የዜግነት ኃላፊነት ለመወጣት ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ለመቀላቀል ወስኛለሁ ያለው ደግሞ ወጣት አበራ ከበደ ነው፡፡
ወጣቶቹን መርቀው ከሸኙ የሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ግርማ አባሴና፤ ወጣቶቹ ሃገር ላቀረበችው ጥሪ ምላሽ በመስጠት ጀግናውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀላቸው ዕድለኛ ናቸው ብለዋል፡፡
ሀገሪቱ ባላት ረዥም ታሪክ ተደፍራ አታውቅም፤ ወደፊትም ቁርጠኛ ልጆቿ እያሉ አትደፈርም ያሉት ደግሞ ሌላው የአካባቢው የሃገር ሽማግሌ አቶ አብደላ ከድር ናቸው፡፡
ለሃገር ጥሪ ምላሽ ከመስጠት በላይ ጀግንነት የለምና ልትኮሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የባሌ ሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገዛኽኝ ደጀኔ በበኩላቸው፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ገንዘብ በማሰባሰብ፣ ስንቅ በማዘጋጀትና ወደ ግንባር በመዝመት አጋርነታቸውን እያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡
በተለይም በርካታ ወጣቶች የመከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ሙሉ ፈቃደኛ መሆናቸው የሚደነቅና ሀገሪቱ ዛሬም ለሉዓላዊነቷ የሚዋደቁ ውድ ዜጎች እንዳላት ያሰየ ተግባር ነው ሲሉም አስታውቀዋል፡፡
በከተማዋ ሠራዊቱን ለመቀላቀል የተዘጋጁት ወጣቶች በሃገር ሽማግሌዎች ምርቃትና ጸሎት የተሸኙ ሲሆን የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ በቃል ኪዳን ተረክበዋል፡፡