የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የስፖርቱ ቤተሰቦች አረጋገጡ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የስፖርቱ ቤተሰቦች አረጋገጡ
አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 29/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የስፖርቱ ቤተሰቦች አረጋገጡ።
በአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን አስተባባሪነት ከ2 ሺህ በላይ የስፖርት ቤተሰቦች የሚሳተፉበት የሶስት ቀናት የደም ልገሳ መርሃ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች፣ የብሄራዊ ቡድኑ የእግር ኳስ ደጋፊ ማህበር አባላት፣ የፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባላት፣ በኮሚሽኑ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ ሰራተኞችና ስፖርተኞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደማቸውን ይለግሳሉ።
ከደም ለጋሾቹ መካከል የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊ ወጣት ሐብቴ ይልማ ለሰራዊቱ ደሙን በመለገሱ መደሰቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበርና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ለሚፋለመው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ደም መስጠት ኩራት መሆኑንም ተናግሯል።
የህይወት ዋጋ እየከፈለ ለሚገኘው ሰራዊት ደም መለገስ "እንደ ዜጋ ማድረግ ከሚገባን በጣም ትንሹ ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ደጋፊው ወጣት ባንተጊዜ ተስፋዬ፤ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ሃይሎችን ለመመከት ዝግጁ ነን ሲል ተናግሯል።
ለሰራዊታችን ደም ለመለገስ በመቻሌ ኩራት ይሰማኛል በማለት ሁሉም ዜጋ ባለው ነገር ሁሉ ድጋፍ በማድረግና ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም የሀገሩ መከታ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት ብሏል።
ኢትዮጵያ ለየትኛውም ጠላት የማትንበረከክ አገር መሆኗን በማስታወስ የአሁኑ ትውልድም ይህንኑ ታሪክ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ምንያህል ጌታቸው፤ በውጭ ጠላቶችና በሀገር ውስጥ ተላላኪዎች በኩል በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች መደናገር እንደማይገባ ገልጸዋል።
ወጣቶችም ለሀገር ህልውና መጠበቅ ግንባር ድረስ ለመዝመት ተጠባባቂ ሃይል ሆነው መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ስልጠና ምርምር ዳይሬክተር እንግዳወርቅ ዳንኤል፤ የደም ልገሳው የስፖርቱ ማህበረሰብ ለሀገሩ ህልውና መቆሙን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከደም ልገሳ በተጨማሪ ለሰራዊቱ ሌሎች ድጋፎችንም ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ በተግባር በመንቀሳቀስ በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ጨምሮ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ይታወቃል።