በሣምንቱ ከ500 በላይ ኢትዮጵያዊያን ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ ተመልሰዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሣምንቱ ከ500 በላይ ኢትዮጵያዊያን ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ ተመልሰዋል
ሐምሌ 29/2013 (ኢዜአ) በሣምንቱ ከ500 በላይ ኢትዮጵያዊያን ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ የተለያዩ አገራት መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሣምንታዊ መግለጫ አበይት ሣምንታዊ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ክንውኖችን አንስተዋል።
የተመድ የሠብዓዊና አስቸኳይ እርዳታ /ኦቻ/ ኮሚሽን ኃላፊ ማርቲን ግርፍቲ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም በሰሜን ኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታዎች የተኩስ ማቆም እርምጃውን አሸባሪው ህወሓት ባለመቀበሉ የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ መስተጓጎሉን አቶ ደመቀ አስታውሰዋቸዋል።
በአማራና በአፋር ክልሎች በተከፈተ ጥቃት ከ200 ሺህ በላይ ዜጎቸ ቢፈናቀሉም ኦቻን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አላወገዙትም በሚል ተገልጾላቸዋል።
ማርቲን ግርፍቲም ሠብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩና የመንግስትን ተኩስ አቁም እርምጃ ማድነቃቸውን አምባሳደር ዲና አንስተዋል።
በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሠላም ጓድ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረገ መሆኑን፤ ዓላማውም በሠብዓዊ ድጋፍና ገፅታ ግንባታ በመሳተፍ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ጎን መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል።
በምጣኔ ሀብት ረገድ የኢትዮ-ናይጄሪያ የጋራ የንግድ ምክር ቤት ለመመስረት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ከአናይጄሪያ አቻው ጋር መፈራረሙን፤ ይህም ለሁለትዮሽ ትስስር መጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁማል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዘርፍ የዳያስፖራው ለሕዳሴ ግድብ ጠንካራ ተሳትፎ የታየበት መሆኑን ያወሱት ቃል አቀባዩ ለአብነትም በጁባ 80 ሺህ ዶላር፤ በአሜሪካም በቀን 124 ሺህ ዶላር መሰብሰቡን አስታውሰዋል።
አምባሳደር ዲና በሣምንቱ ከ500 በላይ ዜጎች ከምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ የተለያዩ አገራት ከስደት ተመልሰዋልም ብለዋል።