ትውልዱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረገውን ሴራ በማክሸፍ የአባቶቹን የድል ታሪክ መድገም አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረገውን ሴራ በማክሸፍ የአባቶቹን የድል ታሪክ መድገም አለበት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2013(ኢዜአ) ትውልዱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረገውን ሴራ በማክሸፍ የአባቶቹን የድል ታሪክ መድገም እንዳለበት የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጥሪ አቅርቧል።
የማሕበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ሻረው ለኢዜአ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የውጭ ጠላቶች ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተለያዩ ሴራዎችን እየሸረቡ ነው።
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረግ ማንኛውንም አይነት ሴራ አጥብቆ ይታገላል ነው ያለት።
ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዜት የገጠሟቸውን ሀገራዊ ፈተናዎች በመመከት ረገድ አኩሪ ገድል መፈጸማቸውን አስታውሰው፤ የአሁኑ ትውልድም ሀገር ጠብቆ የማቆየት ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
በተለይ ወጣቶች ከኢትዮጵያ አልፎ በተለያዩ ሀገራት ሰላም በማስከበር አርአያ ከሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጎን መቆም እንዳለባቸውም ነው ያነሱት።
"እኛ ኢትዮጵያዊያን ሀገራችንን ለማፍረስ የሚደረገውን ሴራ በአንድነት መመከት አለብን" ሲሉም አቶ በቀለ ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህወሃት አሸባሪ ቡድን እያከናወነ ያለውን ሀገር የማፍረስ ተግባር በትክክል ሊገነዘብ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የማሕበሩ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ትእግስት ኃይሌ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች አሸንፋ በነጻነት የኖረች ሀገር መሆናን አስታውሰዋል።
ለዚህ ደግሞ ጀግኖች አባቶቻችን ታሪክ የሚያወሳው መስዋዕትነት ከፍለዋል ያሉት ወይዘሮ ትእግስት፤ የአሁኑ ትውልድም ሀገር በመጠበቅ ረገድ የአባቶቹን የድል ታሪክ መድገም እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚደረገው ሩጫ በምንም አይነት መልኩ ሊሳካ እንደማይችልም ጨምረው ገልጸዋል።