ያጋጠሙ ችግሮች ውስብስብ ቢሆንም በዓመቱ በሁሉም መስኮች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ያጋጠሙ ችግሮች ውስብስብ ቢሆንም በዓመቱ በሁሉም መስኮች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል
አዳማ ፤ ሐምሌ 28/2013 (ኢዜአ) ያጋጠሙን ችግሮች ውስብስብ ቢሆንም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሁሉም መስኮች አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
በየደረጃው ያሉት የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች የተሳተፉበት የስራ ግምገማ መድረክ በአዳማ አባ ገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
ምክትል ከንቲባዋ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ፤ በአስተዳደሩ በዓመቱ ከተመዘገቡ የልማትና የፖለቲካ ስኬቶች ባሻገር አሸባሪው ህወሃት ሀገሪቱን ለማፍረስ ከጠላት ጋር አብሮ ያሰበውን የጥፋት ሴራ በማክሸፍ ለውጤት የበቃንበት ነው ብለዋል።
አባቶቻችን ደማቸውን አፍሰሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ያስረከቡንን ሀገር ለማፍረስ የሚያደርገውን አፍራሽ ሴራ በማክሸፍና በቀጣይ የተጀመረውን ዘመቻ በድል ማጠናቀቅ አንዱ የመድረኩ ትኩረት ነው ያሉት።
የውክልና ጦርነቱን ለማስወገድ በሚቻልበት ሂደትና አቅጣጫ ላይ መድረኩ ትኩረት እንደሚያደርግም አስረድተዋል።
ዛሬ የሚንገኝበት ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ መድረኩ አመራሮችን ቀጣይ ተልዕኮን በብቃት እንዲወጡ ለማዘጋጀት ያለመ ነው ሲሉ አመላክተዋል።
የ2013 በጀት ዓመት የተገኙ ውጤቶችና ያገጠሙ ችግሮችን በመገምገምና ተሞክሮ ተወስዶበት ለአዲሱ በጀት ዓመት መነሻ ዕቅድና የአፈፃፀም አቅጣጫ ይቀመጣል ብለዋል ።
በተለይም ተላላኪ ህወሃት ርዝራዥ ጨምሮ የሌሎች ባንዳዎችን ሴራና ዓላማ ለማምከን ብሎም ከነ አስተሳስባቸው ለመቅበር ህዝቡ እያደረገ ያለውን ርብርብና የጀግንነት ወኔ ለተጀመው የህልውና ዘመቻ ትልቅ ስንቅና አቅም መሆኑን ወይዘሮ አዳነች አስታውቀዋል።
አሁንም ህዝቡ ከመንግሥትና ከጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን እያሳየ ያለውን ታላቅ ተጋድሎ በአግባቡ ማስተባበርና መምራት ይጠበቅብናልም ብለዋል።
ወይዘሮ አዳነች እንዳብራሩት፤ በአዲሱ በጀት ዓመት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፍላጎትና ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሚደረገው ርብርብ ባለፈ የህዳሴ ግድብና የሀገር ደህንነት ጉዳይ በበጀት ዓመቱ ቀዳሚ ትኩረት የሚያገኙ ናቸው።
በተለይም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ጉድለቶችን በማጥራት የወቅቱን ፈተና በብቃት ለመወጣትና ህዝቡ የሰጠንን አደራ ለማሳካት ከእያንዳንዳችን ብዙ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የልማት ዕቅዶቻችንን ያሳካነው ኮሮና በኢኮኖሚ ላይ የሳደረውን ጫና ተቋቁመን ነው ያሉት ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለስ ዓለሙ ናቸው።
በተያዘው የበጀት ዓመት በከተማዋ ማህበረሰብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረው የኑሮ ውድነት፣ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ላይ አሁንም ልዩ ትኩረት ሰጥተን መስራት የሚጠበቅብን ሲሉም አቶ መለስ አስታውቀዋል።
ለቀጣይ ሶስት ቀናት በሚቆየው የግምገማው መድረክ ከአዲስ አበባ አሰተዳደር ሁሉም ክፍለ ከተሞችና የወረዳዎች አመራሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ከአዳማ ዘግቧል።