ቀጥታ፡

አሸባሪው የህወሃት ርዝራዥ እየፈጸመ ያለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አለም አቀፍ የጦር ወንጀል ነው

ደባርቅ፤ ሐምሌ 28/2013 (ኢዜ) አሸባሪው የህወሃት ርዝራዥ ህጻናትን ለጦርነት መማገድን ጨምሮ እየፈጸማቸው ያሉ የተለያዩ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች አለም አቀፍ የጦር ወንጀል ነው ሲሉ በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

በቡድኑ የጥፋት ተልዕኮ ከሚደግፉ አንዳንድ የውጭ ሀገራት ጫናን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማላቀቅ ኢትዮጵያዊያን ጠንካራ አንድነት በመፍጠር መትጋት ይኖርብናል።

በደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ምሁር  ጌታቸው ወረታው ፤ ምዕራባውያን በወንጀል የተጨማለቀውን አሸባሪ ቡድን የብሄራዊ ጥቅሞቻቸው ማሳኪያ እንዲሆን አይዞህ በማለት መልሶ ለጥፋት እንዲነሳ እያገዙ ነው ብለዋል።

የህውሃቱ ዘመነ መንግስት ለምዕራባውያን ፍላጎት የተመቸ ነበር ያሉት ምህሩ፤ የለውጡ መንግስት እንደፈለጉት ሊሆን ባለመቻሉ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደር እየሞከሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለብሄራዊ አንድነት እንሰራለን ያሉ የበለፀጉ አንዳንድ ሃገራት በአሸባሪነት ከተፈረጀ ቡድን ጋር መተባበራቸው ተቀባይነት የለውም።

አሸባሪው የትህነግ ርዝራዥ መንግስት የወሰደውን የተኩስ አቁም ጥሶ ጦርነት በከፈተበት ወቅትና መንግስት የጥሞና ጊዜውን አክብሮ ባለበት ጊዜ በሰብዓዊ አቅርቦት ስበብ በሱዳን በኩል ያለክልከላ መንገድ ክፍት ሊሆን ይገባል ተብሎ የቀረበው ጥያቄ ውድቅ መደረጉ ተገቢ ነው።

ቡድኑ ህጻናትን በጦርነት በማሳተፍ መማገዱ አለም አቀፍ ወንጀል መሆኑን ያመለከቱት ምሁሩ ፤ የኢትዮጵያ ችግር በራሳችን መፍታት እንችላለን ብለዋል።

ከዚህ ጫና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማላቀቅ ኢትዮጵያዊያን ጠንካራ አንድነት በመፍጠር  መትጋት ይኖርብናል ሲሉ ምሁሩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አብራርተዋል።

በዩኒቨርሲቲው  የታሪክ ምሁር የሆኑት  ጡሬ መኳንንት በበኩላቸው፤ትህነግ  በስልጣን በነበረበት ወቅት አንዱን ብሄር ከሌላው  በማጋጨት ሃገር ለማፍረስ የነበረው እድል ሲከሽፍበት  አሁን በጦርነት ለማዳከም  እየጣረ መሆኑን አስረድተዋል።

የህውሃት ርዝራዥ ኢትዮጵያ የተረጋጋች፣ ዴሞክራሲ፣ ሰላምና ፍትህ የሰፈነባት ጠንካራ  እንዳትሆን ከሚፈልጉ ከአንዳንድ የውጭ  ሃገራት ጋር ተባብሮ እየሰራ ይገኛል።

አሜሪካና ተባባሪዎቿ ወንጀለኛውን ለህግ ማቅረብ ሲገባ  በጣልቃ ገብነት በምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ትግራይ ክልል ያለ ገደብ መተላለፊያ እንዲከፈት እየቀረበ ያለው ጥያቄም ግጭቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበት ነው።

ይህም ሆኖ አሸባሪው የትህነግ ርዝራዥ በፈፀመው ወንጀል በዓለም አቀፍ ህግ እንዲቀጣ የጥፋት ድርጊቱን  ማጋለጥና አንድነታችን መጠበቅ ይኖርብናል ሲሉ ነው ምሁሩ የተናገሩት።

ህውሃት  እሱ በሚፈልገው መንገድ ያልመራት ኢትዮጵያ ትፍረስ በሚል እብሪት  ከመሪነት ወርዶ አሸባሪ ቡድን ሆኗል ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህግ ምሁር  መኳንንት ዱቤ  ናቸው።

አሸባሪ ቡድኑ በዓለም አቀፍ ህጎች የተከለከሉ ድርጊቶችን እየፈፀመ መሆኑን በተለይም ህፃናትን አደንዛዥ እፅ በመጠቀም ለጠርነት መማገዱን ጠቅሰዋል።

በማይካድራ ዘርን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ ፣የሰራዊት አባላትን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደልና የጦር ትንኮሳ በማድረግ የፈጸማቸው አለም አቀፍ ወንጀሎች ናቸው።

ቡድኑ ተደራራቢ ወንጀሎችን ከመፈፀም አልፎ ሃገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ባለበት በዚህ ወቅት ለሰብዓዊ መብት በመከበር ዋስትና ነኝ የሚሉ አንዳንድ የውጭ ሀገራትና ተቋማት በዝምታ ማለፋቸው የሚያሳዝን ነው።

እንደ አሜሪካና እንግሊዝ ያሉ ሃገራት ለአሸባሪው በመቆም  በኢትዮጵያ ላይ  እያደረሱ  ካለው  ጫና ለመላቀቅ በተጨባጭ ማስረጃ እውነታውን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማሳወቅ ከሁላችንም እንደሚጠበቅ ተመልክቷል።

በአሸባሪነት የተፈረጀው የትህነግ ርዝራዥ ቡድን  ህጻናትን ለጦርነት በመማገድና ሌሎችንም የፈጸማቸው ኢ-ሰብአዊ የጥፋት ድርጊቶች በአለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቀው መሆኑን ምሁራኑ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም