አሸባሪው ህወሃት በዘመኑ ሁሉ ሃሰተኛና የተምታቱ መረጃዎችን ሲያሰራጭ የኖረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት በዘመኑ ሁሉ ሃሰተኛና የተምታቱ መረጃዎችን ሲያሰራጭ የኖረ ነው
ሐምሌ 28/2013 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በዘመኑ ሁሉ ሃሰተኛና የተምታቱ መረጃዎችን ሲያሰራጭ እንደኖረ ሕዝቡ መገንዘብ አለበት ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ሕዝቡ በመንግስት ይፋ የሆኑ መረጃዎችን በመከታተል ራሱን ከሃሰተኛ መረጃ መጠበቅ እንዳለበት ጠቁመዋል።
አሸባሪው ቡድን የፌዴራል መንግስት መቀሌንና የተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ለቅቆ ከወጣ ማግስት ጀምሮ ሀሰተኛና አደናጋሪ መረጃዎችን በራሱና በዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ የትስስር ገፆች በኩል እየለቀቀ ይገኛል።
መንግስት ሰብዓዊነትን ማዕከል አድርጎ በክልሉ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ቢያደርገም አሸባሪው ቡድን በውጊያ አሸንፎ ከተደበቀበት ዋሻ የወጣ በማስመሰል የተለያዩ መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ ነው።
በመቀጠልም 'ሳይውል ሳያድር' የተናጥል የተኩስ አቁሙን ወደ ጎን በማድረግ ከህጻናት እስከ አዛውንት በውጊያ አሰልፎ በአዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ትንኮሳ እየፈጸመ ይገኛል።
በዚህ ምክንያት በትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ከተሞችን 'ተቆጣጠርኩ'፣ የኢትዮ ጂቡቲ መንገድ 'ተቆጣጠርኩ' እያለ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት በህዝቦች ዘንድ መደናገርን እየፈጠረ ነው።
እነዚህን የሀሰተኛ መረጃዎች ለማሰራጨት በተለያዩ መልኩ የጥቅም ተጋሪው በሆኑ የአገር ውስጥና የውጪ መገናኛ ብዙሃንና 'አክቲቪስቶችን' እየተጠቀመ ይገኛል።
አሸባሪው ሕወሃት በሚያወጣው የተሳሳተና አደናገሪ መረጃ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ሕዝብ ለጥርጣሬ እየተደረገ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ኃላፊዎች ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንደነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ዘርይሁን ገብረእግዚያብሔር እንደሚሉት፤ የአሸባሪ ሕወሃት ሁሉ ነገሩ በውሸት ላይ የተመሰረተ ነው።
ቡድኑ ከመሰረቱ ጀምሮ ሀሰትን መሰረት አድረጎ ሲያደነግር መኖሩን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሀሰት ትርክት ለመከፋፈል ሲጥር እንደነበር ጠቁመዋል።
በመሆኑም ሕዝቡ አሸባሪው የሚያሰራጨውን የውሸት መረጃ ወደ ጎን መተው እንዳለበት አመልክተው፤ በመንግስት በኩል የሚወጡ ትክክለኛ መረጃዎችን ማመን መቻል እንዳለበት ተናግረዋል።
የህዳሴ ፓርቲ (ህዳሴ) ኢንጅነር ሱራፌል እሸቱ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ መንግስት ለዚህ ጉዳይ ብሎ ያዘጋጃቸውን ትክክለኛ የመረጃ ምንጮችን መከታተል፣ መቀበልና ማመን ያስፈልጋል።
ከሁሉም በላይ ዓለም ላይ የተከለከለውን ህፃናትን ለውትድርና እያሰለፉ ትክክለኛ ማስመሰላቸው የሚያሳዝን ተግባር እንደሆነም ጠቅሰዋል።
መንግስትም ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ በመስጠት በኩል ያለበትን ክፍተት ማሻሻል እንደሚገባው የጠቆሙት ደግሞ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ጸሐፊ አቶ ክፍለማሪያም ሙሉጌታ ናቸው።
አሸባሪው ቡድን እውነትን የማያውቅ መሆኑን ህዝቡ መረዳት እንዳለበት ጠቁመው፤ ሀሰተኛ ዜናዎችን ከማራባትና ማባዛት መቆጥብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ፓርቲዎቹ በዚህ ጉዳይ ለአባሎቻቸው አስፈላጊውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች ፓርቲዎችን ይህንኑ ተግባር እንዲያከናውኑም ጠይቀዋል።
በተለያየ ዓለም የሚኖሩ የአሸባሪው ህወሃት ተከፋይ ደጋፊዎች 'የበሬ ወለደ' ሀሰት ወሬዎችን ማሰራጨታቸውን እንደቀጠሉበት ነው።