የአሸባሪው ህወሃት አመራሮች በትግራይ ታዳጊዎች ላይ የጦር ወንጀል እየፈጸሙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪው ህወሃት አመራሮች በትግራይ ታዳጊዎች ላይ የጦር ወንጀል እየፈጸሙ ነው
ሰመራ፤ሐምሌ 28/2013(ኢዜአ) ታዳጊ ህይወት ሀዋዝ ባልጠበቀው ሁኔታ አድዋ ከወላጆቹ ጋር በሚኖርበት ቤት የቀበሌ አመራሮች በመምጣት ትፈለጋለህ ብለው ሲወስዱት እሱም ቤተሰቡም በጣም ደንግጠው እንደነበረ ይናገራል።
ምንም የጦርነትም ሆነ የውጊያ እውቀት ሳይኖረው ከሌሎች የአካባቢው ታዳጊዎች ጋር ወደ ግንባር ሲልኩት መቃወም ባይችልም አብሮ እንደማይዘልቅ ቀድሞ ወስኗል።
በዚህም ግንባር ላይ እያለ ከጦርነቱ ለማምለጥ ሲሞክር ተመቶ ቆስሎ መያዙን ተናግሯል።
"በዚህ ዘመን ፍትሃዊ ላልሆነ ጦርነት የዳረጓቸዉ አካሎች በህዝብ ላይ እየፈጸሙ ያሉት ተግባር የሚያሳፍር በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ሊቃወማቸዉ ይገባል" ብሏል።
ከሽሬእንዳስላሴ የመጣው ታዳጊ ገብረሊባኖስ የማነ ደግሞ "ትግራይ ተወራለች ነጻ ማውጣት አለብን" በሚል ከቤተሰቦቹ ነጥለው አስገድደው ወደ ጦርነት እንዳስገቡት ይናገራል።
የራሳቸውን ልጆች በተሻለ ሁኔታ እያኖሩ የደሃ ልጆችን ለሞት የሚዳርጉትን የአሸባሪው ህወሃት አመራሮች ህዝቡ መታገል አለበት በማለትም ቁጭቱን ይገልጻል።
በጦርነቱ በርካታ ታዳጊዎች ሲጎዱ ቀሪዎቹ የተሳካላቸው ደግሞ ማምለጥ መቻላቸውን ገልጾ፤ እሱም በአፋር በኩል ተገደው በገቡበት ጦርነት ሲሸነፉ መሳሪያዉን ጥሎ ለማምለጥ ሲሞክር መያዙንም ተናግሯል።
ከመቀሌ ከተማ ተገዶ ወደ ጦርነቱ የገባው ታዳጊ ገብረ አርአያ ደግሞ ለውጊያ በቂ ስልጠና ሳይወስዱ የተወሰነ የመሳሪያ መፍታትና መግጠም ሒደትን ብቻ አይተው በአፋር ግንባር እንደተላኩ ይናገራል።
"መሳሪያ ከቆሰሉ ሰዎች ወይም ከመከላከያ ነጥቀን እንሰጣችኋለን" ተብለዉ በባዶ እጃቸው ወደ ጦርነቱ ሲገቡ ተደናግጦ ህይወቱን ለማዳን ሾልኮ ለማምለጥ ሲሞክር እንደተያዘም ያስረዳል።
"የአመራሮቹ ልጆች በሰላም ተቀምጠዉ እኛን አታለዉ ወደ ጦርነት ይዘዉን ገብተዋል" የሚለው ታዳጊው ድርጊቱን ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ሊያወግዙት እንደሚገባ አስረድቷል።
በግንባሩ ህብረሰተቡን በማስተባበር ስራ ላይ የሚገኘዉ የክልሉ ማረሚያ ቤት ምክትል ኮሚሽነር አቶ መሀመድ አህመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአሸባሪው ህወሃትን የጥፋት ሴራ የማምከኑ ስራ በተሳካ ሁኔታ ቀጥሏል።
"ይሁንና ሞት አፋፍ ላይ የሚገኘዉ የህወሃት አሸባሪ ቡድን እስትንፋሱን ለማራዘም ዛሬም ገና አጥንታቸዉ ያልጠነከረ ለጋ ታዳጊዎችን ከትግራይ እናቶች እየነጠቀ የጦርነቱ ሰለባ እያደረገ ይገኛል" ብለዋል።
በዚህ ጥቃት የራሱን ስልጣንና የጥፋት ተልዕኮ እንዲያሳኩ በገፍ የሚልካቸው ታዳጊዎችና ሴቶች ምኞቱን እንደማያሳኩለት ገልጸው፤ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን አጠናክረው የጀመሩትን ትግል እንዲያስቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ቀደም ሲል በአፋር ክልል ፈንቱ ረሱ በተባለ ስፍራ አሸባሪው ህወሃት ያሰለፋቸውና በጸጥታ ሃይሎች እየተያዙ ያሉ በርካታ ታዳጊዎችን በማነጋገር የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መዘገቡ ይታወሳል።