የህወሃት አሸባሪ ቡድን ካልጠፋ በስተቀር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር እንደማይችል አሜሪካ ልትገነዘብ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃት አሸባሪ ቡድን ካልጠፋ በስተቀር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር እንደማይችል አሜሪካ ልትገነዘብ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 28/2013 (ኢዜአ) የህወሃት አሸባሪ ቡድን ካልጠፋ በስተቀር በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር እንደማይችል አሜሪካ ልትገነዘብ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት።
የዲያስፖራው ማህበረሰብ ከመቸውም ጊዜ በላይ እጅ ለእጅ ተያይዞ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች አሸንፋ እንድትሻገር የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አምሳሉ ካሰው፤ ምእራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱት ጫና የራስን ጥቅም ከማስጠበቅ የመነጨ እንጂ ለኢትዮጵያውያን አስበው እንዳልሆነ ይናገራሉ።
የምእራባውያን ዋነኛ ፍላጎት በኢትዮጵያ ታዛዥ መንግስት ማቆም መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን የአሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ለሀገር ሉዓላዊነትና ለዜጎች ክብር የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት "ያለማንም ጣልቃ ገብነት የራስን ችግር በራስ አቅም መፍታት" የሚል አዲስ እሳቤ ይዞ መምጣቱ ለምእራባውያን ብዙም የተመቸ ሆኖ አልተገኘም ነው ያሉት።
ከዚህ አኳያ ምእራባውያን የተቻላቸውን ጫና በማድረግ የኢትዮጵያን መንግስት አቋም ማስቀየር እንደሚሹ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም መስፈን ከፍተኛ ሚና ያላት መሆኗን የገለጹት አቶ አምሳሉ በኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር ቀጠናው እንዳይረጋጋ ያደርጋል ብለዋል።
በዓለም ጂኦ-ፖለቲካ ስትራቲጅክ ሚና ያለው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና አለመረጋጋት ከአፍሪካ በተጨማሪ ምእራባውያንን እንደሚጎዳም ነው የተናገሩት።
አሸባሪው ህወሃት የሚያደርጋቸው ትንኮሳዎች ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዳይሰፍን እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የሽብር ቡድኑ መወገድ ለቀጠናው ዘላቂ ሰላም ሚናው የጎላ መሆኑን አሜሪካን ጨምሮ ምእራባውያን እንዲገነዘቡት እየሰራን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን የራሱን ህይወት ለማቆየት ታላቅ ተስፋ ያለችውን ህጻናት በጦርነት እየማገደ መሆኑን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በቅርቡ በአሜሪካን ኮንግረስ የጥቁር አሜሪካውያን አባላት ጉባኤ ሰብሳቢ ከሆኑት ካረን ባስ ባደረጉት ውይይት የህወሃት አሸባሪ ቡድን ህጻናትን በጦርነት እያሰለፈ መሆኑን በሚመለከት አስፈላጊውን መረጃ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ አባላት አሜሪካ ዓለም አቀፍ ወንጀል እያስፈጸመ ካለው የሽብር ቡድን ጋር መተባባር እንደሌለባት አጽኖት ሰጥተው መናገራቸውንም ነው አቶ አምሳሉ የገለጹት።
በዚህም ኢትዮጵያን በሚመለከት የአሜሪካን መንግስት ያወጣው የውሳኔ ሃሳብ 'ኤች አር ኢ ኤስ 445' ሳይጸድቅ እንዲዘገይ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
"አሜሪካ የኢትዮጵያ ወዳጅ እንጂ ጠላት አይደለችም" የሚሉት አቶ አምሳሉ፤ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር የሚፈልጉ በባይደን አስተዳደር ውስጥ ያሉ ጥቂት ግለሰቦች እንጂ የአሜሪካ ፖለቲካኞች አይደሉም ብለዋል።
"የገጠመን ችግር ወቅታዊ በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን መስራት አለብን፤ ሁኔታዎችም በጥሩ መልኩ እየተቀየሩ ነው" ብለዋል።
ዲያስፖራው እጅ ለእጅ ተያይዞ ለኢትዮጵያ እየሰራ በመሆኑን ገልጸው፤ በአሜሪካ የሚኖሩ አፍሪካውያን ዲያስፖራዎችም ከኢትዮጵያ ጎን መሆናቸውን በተግባር እየገለጹ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከር ለሀገራቸው ብርታት መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።