ዲያስፖራው ለህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ በተዘጋጃው ዲጂታል የክፍያ ስርዓት ላይ በስፋት እየተሳተፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲያስፖራው ለህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ በተዘጋጃው ዲጂታል የክፍያ ስርዓት ላይ በስፋት እየተሳተፈ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሀምሌ 28/2013 ዲያስፖራው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ በተዘጋጃው ዲጂታል የክፍያ ስርዓት ላይ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገለጸ።
ባንኩ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና ከህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ጋር በመተባበር የክፍያ ስርዓቱን የማስተዋወቂያ መርሃ-ግብር አካሂዷል።
የክፍያ ስርዓቱ ከአገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ የሚያደርጉት ድጋፍ የበለጠ ለማሳደግ ያለመ ነው።
የክፍያ መተግበሪያውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 'ኤግል ላይን' ከተሰኘ ኩባንያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሲሆን ዳያስፖራው ማህበረሰብ ባለበት ሆኖ በስልኩ አልያም በኮምፒተር በመታገዝ ድጋፍ እንዲያደርግ ያስችላል ።
በዚህም ዳያስፖራው ከ1 እስከ 10 ሺህ ዶላር ድረስ ድጋፍ ማድረግ የሚችል ሲሆን ከ100 ዶላር በላይ ድጋፍ ለሚያደርጉ ደግሞ የምስክር ወረቀት ይሰጣቸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ ከዚህ ቀደም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትወልደ ኢትዮጵያዊያን አመቺ ሆነ የክፍያ ስርዓት አለመኖሩ ዲያስፖራው በሚፈለገው ልክ ለግድቡ ድጋፍ እንዳያደርግ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል።
ከሳምንት በፊት ዲያስፖራው በቀጥታ ድጋፍ ማድረግ የሚችልበት ስርዓት ተግባራዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ አበረታች ድጋፍ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑም ድጋፉ እንዲጠናከርም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ዳያስፖራው ማህበረሰብ ለግድቡ የሚያደርገው ድጋፍ በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ለአብነት አንስተዋል።
ከዚህም ውስጥ በ2013 ዓ.ም ብቻ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ከቦንድ ግዥ፣ ከስጦታና ሌሎች ድጋፎች ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡንም ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌትን ተከትሎ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በውጭ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰቡንም አመልክተዋል።
በቅርቡ ይፋ በተደረገው "ማይ ገርድ" ዲጂታል ድጋፍ ማድረጊያ ክፍያ ስርዓት ከ140 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የግድቡ ግንባታ በሚፈለገው አግባብ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
ግድቡ በቅርቡ የመጀመሪያ ዙር ኃይል የማመንጨት ስራውን እንደሚጀምር የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ግድቡ ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ "ግድቡ ኢትዮጵያን ከጥገኝነት የሚያላቅቅና ሉአላዊነቷን የሚያረጋግጥ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆነው ግድብ እንዲጠናቀቅ ብዙ ሥራ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ነው ብለዋል።
ሌሎች ተቋማት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ፈለግ እንዲከተሉም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለግድቡ ግንባታ ማስፈጸሚያ ተግባራዊ በተደረጉ የተለያዩ የሃብት ማሰባሰቢያ አሰራሮች አማካኝነት ከ102 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ማሰባሰብ መቻሉን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።