የኢትዮጵያ እናቶችን ጡት የማጥባት ጥሩ ተሞክሮ ማጠናከር የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል- ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እናቶችን ጡት የማጥባት ጥሩ ተሞክሮ ማጠናከር የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ይደረጋል- ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ሐምሌ 28/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ እናቶችን ጡት የማጥባት ጥሩ ተሞክሮ እንዲጠናከር ለማስቻል ጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር ስምምነት ተፈራረመ።
ዓለም አቀፉ ጡት የማጥባት ሳምንት “ጡት ማጥባትን መጠበቅ፣ የጋራ ሃላፊነት!!” በሚል መሪ ሃሳብ ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል።
ጤና ሚኒስቴር ጡት ማጥባት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ በተገቢው መልኩ እንዲከናወን የሚያስችሉ እድሎችን ለማመቻቸት የሚያስችል ስምምነት ከአጋር አካላት ጋር ተፈራርሟል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የኢትዮጱያ እናቶች ከጥንት ጀምሮ ጥሩ የሚባል ጡት የማጥባት ልምድና ባሕል አላቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ 97 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት በማጥባት ያሳድጋሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ክብደታቸው ከሚጠበቀው በታች ሲሆን እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ከ6 ሚሊዮን በላይ ህጻናት የቀነጨሩ ናቸው።
ከ1 ሚሊዮን በላይ ህጻናት ደግሞ የቀጨጩ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በመሆኑም የእናቶች ጡት የማጥባት ጥሩ ተሞክሮ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲደገፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር መሰረት ገልጸዋል።
ለዚህም ስኬት ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ፣ ከኢትዮጵያ ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን፣ ከአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽንና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን ገልጸዋል።
በስምምነቱ መሰረት እናቶች ከመውለዳቸው በፊት ጡት ለማጥባት የሚያስችላቸውን የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዲያዳብሩና የተሻለ እውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ይሆናል።
በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ያሉና የሚያጠቡ እናቶች የሚደገፉበትና በምግብ እጥረት ምክንያት ልጆቻቸውን ማጥባት እንዳያቋርጡ ማገዝንም ስምምነቱ ያካትታል።
በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ሚስስ አደል ኮደር፤ የኢትዮጵያ እናቶች ጡት የማጥባት ልምድ ለሌሎች አገሮች መጋራት ያለበት ትልቅ ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።
ሆኖም የእናቶች የስነ-ምግብ ስርአትና ልጆቻቸውን የማጥባት ሂደታቸው መለወጥና ማሻሻል አለበት ብለዋል።
ለዚህም ጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት ያደረገው ስምምነት አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ዩኒሴፍ አስፈላጊውን የፋይናንስም ሆነ የስልጠና ድጋፎችን በማድረግ የእናቶችን ጡት የማጥባት ልምድ ሳይንሳዊ ዘይቤን ተከትሎ እንዲቀጥል እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስለጣን የምግብ ተቋማት ኢኒስፔክሽን ዳይሬክተር በትረ ጌታሁን፣ እናቶች ለልጆቻቸው የታሸጉ የወተት መርቶችን ከማጠጣት ይልቅ ጡታቸውን እንዲያጠቡ መክረዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ ሜይ 21/1981 የወጣውን የህጻናት ወተት ለገበያ ሊቀርብበት የሚገባውን መመሪያ ኢትዮጵያም እየተገበረችው ቢገኝም ካለው አሁናዊ ሁኔታ አንጻር ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል።
በሶስት የምግብ መመሪያዎች ውስጥ በማካተት ሲተገበር መቆየቱን ጠቅሰው ያልተካተቱና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማድርግ መመሪያውን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የጡት ማጥባት ሳምንት በዓለም ለ30ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።